post-thumb

ሀሰተኛ ደብዳቤዎችን እንደ ማሳመኛ የሚጠቀመው የማጭበርበሪያ ስልት!

በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ወደ ካናዳ፤ አውሮፓ፤ ጨምሮ ሌሎች የውጭ ሀገራት እንልካለን የሚሉ አሳሳች ማስታወቂያዎችን በተደጋጋሚ ሲሰራጩ ይስተዋላሉ። እነዚህ አሳሳች ማስታወቂያዎች በስፋት ህጋዊ ነን በማለት ከተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ የተጻፈላቸው በማስመሰልና ሐሰተኛ ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት ዜጎችን የማታለል ሥራ ይሰራሉ።

እነዚህ ደብዳቤዎች የተቋማትን ደብዳቤዎች  በመቀየር የራሳቸውን ስም እና ይዘት በማስገባት የሚፈጠሩ ሐሰተኛ ደብዳቤዎች ሲሆኑ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለማሳመን ይቀርባሉ። ከመንግሥት፣ ከኤምባሲዎች ወይም ከውጭ ታዋቂ አሰሪዎች ጋር ጥብቅ ቅርበት እና አጋርነት እንዳላቸው በዚህም ቶሎ ሥራ እንደሚያስገኙና ከፍተኛ ደሞዝ እንደሚያስከፍሏቸው ያሳምኗቸዋል።

በዚህም ተታለው በርካቶች ገንዘባቸው በአጭበርባሪዎች ተወስዷል። ከ2000 ብር ጀምሮ በመቶ ሺ ብሮች መክፈላቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ። ለማጣራት የተመለከትናቸው ደብዳቤዎች በሐሰት የተፈበረኩ ስለመሆናቸው ደብዳቤዎቹ ላይ የሚገኙት ምልክቶች በራሳቸው በቂ ማስረጃ ሆነው ይገኛሉ። 

 

 

ከላይ በምስሎቹ በተመለከታችኋቸው ደብዳቤዎች መሰረት ይዘቶቹ በተለይም ማኅተም እና ፊርማዎቹ ከሌላ ደብዳቤ ላይ ተቆርጠው የተቀመጡ ስለመሆናቸው ማስተዋል ይቻላል። በተጨማሪም ማህተም ሲመታ ከጹሑፉ ላይ ሲሆን እዚህ ላይ ግን ማህተሙ ከተመታ በኋላ የተፃፈ ደብዳቤ መሆኑ ሌላው ደብዳቤዎቹ የተነካካ ይዘት እንዳላቸው ማሳያ ነው።ይህ ብቻም ሳይሆን ጹሁፎቹም ከጀርባቸው ላይ ያለው የደበዘዘ ምልክት መኖሩ የደብዳቤዎቹ ይዘት ወጥ አለመሆኑንና የተጨመረ ይዘት መኖሩ ደብዳቤዎቹ ሐሰተኛ መሆናቸውን አመላካቾች ናቸው፡፡ ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር በሐሰት የተሰራውን ደብዳቤ እና ትክክለኛ ደብዳቤ ፎቶ ፎረንሲክን ተጠቅመን ልዩነታቸውን መመልከት እንችላለን፡፡

 

ከላይ በምስሉ እንደምትመለከቱት የመጀመሪያው ምስል ላይ በተለይ ማኅተም ያረፈበት፤ ሎጎዎች የተቀመጡበት እና ቀን እና ቁጥር ያለበት ክፍል የተለያየ የቀለም ይዘት ያላቸው ሲሆን ይህም በፎቶ ፎረንሲክ ምርመራ የተነካካ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ከጎን ያለው ትክክለኛ ደብዳቤን ፎቶ በማንሳት የቀረበ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ወጥነት ያለው ሆኖ ይታያል፤ ይህም ደብዳቤው ትክክለኛ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

የማጭበርበሪያ መንገዶቹ ግን ደብዳቤዎቹ ላይ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ሌሎች የማታለያ መንገዶችንም ጨምሮ የሚሰራ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተመሳሳይ አይነት ይዘት የሚያስተዋውቁ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በቲክቶክ ላይ ሰዎችን ለማሳመን በሚል የሀሰት ዐውድ በመፍጠር የተለያዩ መረጃዎች ይሰራጫሉ።

 

በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ምስል የተወሰዱት ከቲክቶክ ገጽ ላይ ሲሆን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ እንዲሁም ሪፖርት ሲያቀርቡ የተናገሩትን  በመቁረጥና በመነካካት ከጀርባው ይሄንኑ ደብዳቤ በማድረግ ለማሳየት ይሞክራሉ። በተመሳሳይ በተለያዩ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ሽፋን ያገኙ ዘገባዎችን በመቆራረጥ ለእነሱ የሚስማማውን ብቻ ሰዎች እንዲያደምጧቸው ያደርጋሉ። 

አብዛኛውን ጊዜም እንደዚህ አይነት መረጃዎች ሲለቁ አብረው አካውንት እና ስልክ ቁጥር ያስቀምጣሉ። ብዙ ጊዜ ይህንን ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ዓላማቸው የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት እንደሆነ ይታመናል። በዚህም "ቶሎ እንዲወጣላችሁ" ፤ "ወረፋ እንዲፈጥንላቹ" በማለትና መሰል ስልቶችን በመጠቀም ገንዘብ ያስልካሉ።

እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭታቸው ምን ያህል ነው?

በዚህ መልኩ የሚሰሩ ማጭበርበሮች ሥርጭታቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው። ምንም እንኳን መሰረታዊ ዲጂታል እውቀት ያለው ግለሰብ ደብዳቤዎቹንና መረጃዎቹን ለመለየት የሚቸገር ባይሆንም ከተደራሲያኑ ጋር ሲነጻጸር የሚያደርሱት ጉዳትና የሚፈጥሩት ቀውስ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የተወሰኑ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል።

1.  መንግስት በህጋዊ መንገድ የሚልካቸው ዜጎች በመኖራቸው በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ማስታወቂያዎች ይነገራሉ። እነዚህ ማስታወቂያዎች በተለይም በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል ሥራ ፈላጊዎች መንግሥት በዘረጋው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (ለሜስ) እንዲመዘገቡ ጥሪ ያቀርባል፡፡ ይህ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ አጭበርባሪዎቾ በቀላሉ ሰዎችን ለመጥለፍና ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ ማስታወቂያዎቹንና የሥራ ሪፖርቶችን በመጥለፍ ፤ በመቁረጥና ሐሰተኛ ማስረጃዎችን በመጨመር በተለይም ወደ ውጪ መጓዝ የሚፈልጉ ሰዎችን ወደራሳቸው ይስቡበታል፡፡

2.  በኢትዮጵያ ካለው የሥራ አጥነት ችግር አንጻር እንዲሁም ወጣቱ ዘንድ ያለው ወደ ውጪ የመውጣት ጉጉት ሥርጭቱ በአንድ አከባቢ የሚወሰን ብቻ ሳይሆን ሰፊ ሽፋን እንዲኖረው በማስቻሉ ጉዳዩ ከከተማ አልፎ እስከ ገጠር ድረስ የመውረድ አቅም ስላለው ሌላው ስፋቱን የሚያሳይና የጉዳቱን መጠን የሚገልጽ ማስረጃ ነው።

3.  የሚሰሩት ማስታወቂያዎች በአቋራጭ መንገድ የእድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያሳምኑ ስለሆኑ በትክክለኛው መንገድ ተመዝግበው የሚጠብቁ ስራ ፈላጊዎች ጎን ለጎን በአቋራጭ መንገድ እድሉን ለማግኘት እንዲሞክሩ ያደርጋቸዋል። 

4.  ይህን ሥራ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ ሳይሆን ንግድ ፈቃድ አውጥተው፤ ቢሮ ተከራይተው እና ከዚህም ገዘፍ ያለ አሳማኝ ማስታወቂያዎችን የሚሰሩ በርካታ ተቋማት መኖራቸው በራሱ ሰዎችን ይበልጥ ለአጭበርባሪዎች እንዲጋለጡ ያስችላቸዋል፡፡[1]

በተጨማሪም በዚህ የማጭበርበር ሥራ የተሳተፉ ግለሰቦች በርካታ ስለሆኑ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ለተመሳሳይ ማስታወቂያዎች ማረጋገጫዎቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ ?

1.  የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ህጋዊና የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ለማድረግ የተፈራረማቸውን ሀገራት በስም ይጠቅሳል (ሳዑዲ አረቢያ፤ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት፤ ሊባኖስ፤ ኳታር፤ ኩዌት) በተጨማሪም የሥራ ማስታወቂያዎችን በገጾቹ ያወጣል።

2.  ሚኒስቴር መ/ቤቱ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ላይ ፈቃድ ያላቸው የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ዝርዝር ያሳውቃል። [2] የምንመለከታቸው ኤጀንሲዎች በዛ ዝርዝር ላይ መኖር አለመኖራቸውን ማጣራት ያስፈልጋል።

3.  በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቀረበው የውጪ ሃገር ስራ ስምሪት ምንም አይነት ክፍያ የለውም። በአንጸሩ ሀሰተኛ እና አጭበርባሪ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ማስታወቂያዎች ለቪዛ፤ ሥራ ማስኬጃ፤ ለህክምና እና ሌሎች ክፍያዎቸ በሚል ቅድሚያ ክፍያ ይጠይቃሉ፡፡ ዋና ዓላማቸውም ሰዎች ገንዘብ እንዲያስገቡ ማድረግ ነው፡፡

በመሆኑም በዚህ ዜና የተካተቱ ደብዳቤዎች እንዲሁም መሰል ማስታወቂያዎች ለማጭበርበር ተብሎ የሚሰሩ የተፈበረኩ መረጃዎች በመሆናቸው ግንዛቤን ማስፋት ያስፈልጋል።

 


ኅዳግ ፡- 

[1] https://www.facebook.com/100064573006378/posts/pfbid02iDErvLbnYCQFmQB65MZxiTT2zm2yfGHs3979FE2Pfkc1zfWU5jGCy367w9Yc3hcXl/?app=fbl

[2] https://t.me/FDRE_MoLSofficial/2656