ኤሎን መስክ ላይ የመኪና አደጋ እንደደረሰ ተደርጎ የተሰራጨው ሃሰተኛ ዜና
በፈረንጆቹ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ 20 በዓለማችን ቁጥር አንዱ ባለሃብት ኤሎን መስክ የመኪና አደጋ የደረሰበት ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡ ይኸው መረጃ በተለያዩ የፌስቡክ ገፆች ተጋርቶ የነበረ ሲሆን ለምሳሌም ከ25 ሺህ በላይ ተከታይ ያሉት "60 second News" እና 12 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው" Digital Frontina" የፌስቡክ አካውንቶች ተሰራጭቷል። ገፆቹ የኤሎን መስክ ቴስላ ሞዴል X ከነዳጅ መኪና ጋር ከተጋጨ በኋላ በእሳት መቃጠሉንና አደጋው የተከሰተው በግል የልደት ድግስ ላይ ከተገኘ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው በማለት የግለሰቡን የህክምና ምስሎች አያይዘው ለቀዋል።

የሃሰት መረጃው ምን ያህል ሰዎች ጋር ደረሰ?
• በ " 60 second News " የተሰኘ ገፅ በተጋራዉ መረጃ ከ 12 ሺህ በላይ የመውደድ እና የሐዘን ምላሽ ወይም Reactions ሲያገኝ ከ560 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃውንም አጋርተዋል።
• በ "Digital Frontina'' የተሰራጨው ደግሞ 4 ሺህ አከባቢ መውደድ እና 343 መጋራቶችን(share)አግኝቷል።
በዚህም ማለትም መረጃው በፍጥነት እና በቀላሉ ብዙ ሰዎች ጋር እንደደረሰ መረዳት ይቻላል።
በምስሎቹ ላይ በተደረገ ማጣራት የተጋሩት ምስሎች ደረሰ የተባለውን አደጋ የማያሳዩ ናቸው። በዘገባዎቹ ላይ የተለጠፈው የመኪና አደጋው ምስል የተነሳው (የተከሰተው) በዜናዎቹ እንደተጠቀሰው ሳይሆን በፈረንጆቹ መጋቢት 16, 2023 እንደተነሱ በ https://tineye.com/ በተደረገው ማጣራት ተረጋግጧል።
በተጨማሪም በሁለቱ የኤሎን መስክ የአደጋ ምስሎች በትኩረት ብንመለከት አደጋው የደረሰው በተለያየ የፊት ቦታ ላይ እንደሆነና በ https://decopy.ai.com 99.99% Al generated እና በ https://sightengine.com በሰው ሰራሽ አስተውህሎት የተፈጠሩ (የተሰሩ) ምስሎች መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።
ሃሰተኛ መረጃው የተሰራጨበት ዓላማ የኤሎን መስክን ዝና እና ስም በመጠቀም ትኩረት ለማግኘት ወይም ስሜታዊነትን በመጠቀም አስደንጋጭ ምስሎች በፍጥነት እንዲሰራጩ ለማድረግ የተሳሳተ መረጃን በማሰራጨት ግራ ለማጋባት እና ሰዎችን ለማሳሳት በዋናነት ደግሞ በመገናኛ ብዙሃን ላይ መተማመንን ለማዳከም ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
ፀሃፊ: ሃፍታሙ ሓለፎም