ባህላዊ መድሃኒቶችን በተመለከተ የሚሰራጭ የተሳሳተ መረጃ
ባህላዊ መድሃኒቶች ብዙውን ጊዜ በተፈጥሮ ዕፅዋት እና ባህላዊ ልምዶች ላይ የተመሰረቱ ከትውልድ ትውልድ ጥቅም ላይ የዋሉ ህክምናዎች እና መፍትሄዎች ናቸው። እነዚህ መድሃኒቶች ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ መነሻ ስላላቸው በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። የባህል ህክምና በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ሰማንያ በመቶው የሚሆነው ህዝብ ለእለት ተእለት የህክምና ፍላጎቱ የባህል ህክምናን ነው የሚጠቀመው። ከእነዚህ ባህላዊ መድኃኒቶች ውስጥ ወደ 95 በመቶ የሚጠጉት ከዕፅዋት የተቀመሙ ናቸው።
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብዙ ህመምተኞች ባህላዊ መድሃኒቶችን ሲጠቀሙ ሲስተዋል ጥናቶችም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህሙማን የባህል ህክምናን መጠቀም የተለመደ እንደሆነ ያሳያሉ። ለምሳሌ የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚዎች በፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ህክምና ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 26% ያህሉ ከዕፅዋት የተቀመሙ እንደ ሽንኩርትና ዳማከሴ መድኃኒቶች ይጠቀማሉ። [1]
ብዙ ሕመምተኞች ምልክቶችን እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ባህላዊ መድሃኒቶችን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ይዘቱ፣ መጠኑ እና ከታዘዙ መድኃኒቶች ጋር ሊኖር የሚችለው መስተጋብር ብዙ ጊዜ ስለማይታወቅ የደህንነት ስጋቶች አሉ። አንዳንድ ሕመምተኞች እንደ የደም ግፊት ለውጥ፣ የጉበት ችግሮች ወይም ሌሎች አሉታዊ ግብረመልሶች ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች አጋጥሟቸዋል። በኢትዮጵያ በባህል ሕክምና ዙሪያ በምርምርና መረጃ ላይ ከፍተኛ ክፍተት አለ። በሕዝቡ ዘንድ በሰፊው ጥቅም ላይ ቢውልም ደኅንነቱን፣ ውጤታማነቱን እና ከዘመናዊ የጤና አጠባበቅ ጋር ውህደቱን የሚዳስሱ ጥናቶች ጥቂት ናቸው። የሀገር ውስጥ ባህላዊ መድሃኒቶች ብዙ ጊዜ መደበኛ እውቅና እና ቁጥጥር ስለሌላቸው በጥራት እና በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ትልቅ የመረጃ ክፍተት ይፈጥራል።
ይህንን የመረጃ ክፍተት በመጠቀም በርካታ የማኅበራዊ ድረ-ገጾች በባሕላዊ መድኃኒቶች ላይ የተዛቡ መረጃዎችን እያሰራጩ ይገኛሉ። ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ እንሰጣለን በማለት ብዙ ተከታዮችን ይሰበስባሉ። ይህ ቁጥጥር ያልተደረገበት የአሳሳች መረጃ ስርጭት ህብረተሰቡ ደህንነቱን የተጠበቀ፣ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ባህላዊ መድሃኒቶች እና ያልተረጋገጡ ወይም ጎጂ መድሃኒቶችን እንዳይለይ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የተሳሳተ መረጃ የይዘት ትንተና
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስለ ባህላዊ ሕክምና አብዛኛዎቹ የተሳሳቱ መረጃዎች ታማኝነትን ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ሃይማኖታዊ ጭብጦችን ይጠቀማሉ። አብዛኞቹ ለሀይማኖት አባቶች እና መሪዎች የሚሰጥን መሪጌታ ማዕረግ ይጠቀማሉ። ሰዎች እነዚህን ፖስቶች ከሃይማኖታዊ እምነቶች ወይም መሪዎች ጋር ሲገናኙ የበለጠ ማመን ይቀናቸዋል።

ተከታዮቻቸውን በፍጥነት ለማሳደግ የማህበራዊ ሚዲያ ቻናሎች እና ቡድኖች ያለፈቃዳቸው ሰዎችን ወደ ቻናሎቻቸው ያስገባሉ፣ ይህም ብዙ ተጠቃሚዎችን ለእነዚህ የውሸት መረጃ ያጋልጣል። ይህ ዘዴ የተሳሳተ መረጃ በፍጥነት እንዲሰራጭ እና ብዙ ተከታዮችን እንዲያፈሩ ይረዳል፣ ይህም ሰዎች የትኛው መረጃ እውነት እና አሳሳች እንደሆነ ለማወቅ የበለጠ ከባድ ያደርግባቸዋል።
እነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች ማንኛውንም ችግር ማስተካከል እንደሚችሉ ይናገራሉ። እንደ መካንነት፣ የስንፈተ ወሲብ፣ትምህርት ፣ ሀብትን እና መልካም እድልን ማምጣት፣ለወር አበባ ችግር፣ ወይም የጋብቻ እድሎችን ማሻሻል ባሉ ጉዳዮች ላይ ለመርዳት ቃል ይገባሉ።ከጥይት የሚከላከሉ መድኃኒቶች እራሱ አሉን ይላሉ። እነዚህ አጓጊ ተስፋዎች መፍትሄ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን ይስባሉ።
ለምሳሌ የሰው አካል እና የብልት አካልን የሚመስሉ ሥሮችን ወይም እፅዋትን ምስሎችን በመጠቀም የስንፈተ ወሲብን ለመፈወስ መድኃኒት አለን ብለው ይናገራሉ። ነገር ግን ቅርጹ አስፈላጊ ስለመሆኑ ወይም እነዚህ ሕክምናዎች በትክክል እንደሚረዱ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ የለም። ይህ ሰዎችን ለማታለል እና በሐሰት ፈውስ እንዲያምኑ ለማድረግ የሚጠቀሙበት መንገድ ነው።

ነገር ግን በመጀመሪያው ምስል ላይ የሚታየው ተክል Tropical pitcher plant ይባላል። የወንድ ብልት ቅርጽ ስላለው ብቻ ነው እንጂ የተረጋገጠ ስንፈተ ወሲብ የመፈወስ ባህሪያት የሉትም። በተጨማሪም Iriartea deltoidea የተባለ ተክል ምስሎችን ተጠቅመዋል።
በተጨማሪም ህጋዊ ለመምሰል እና የሰዎችን አመኔታ ለማግኘት የውሸት የእውቅና ደብዳቤዎችን ይጠቀማሉ ። እነዚህ ደብዳቤዎች ከትክክለኛው አካል የተገኙ ሲመስሉ ሰዎች ምርቶቻቸው በእውነተኛ ተቋማት የጸደቁ ናቸው ብለው እንዲያምኑ ለማታለል የተነደፉ ናቸው።

ከላይ እንደምናየው እነዚህ ሀሰተኛ የእውቅና ደብዳቤዎች ማህተም ከሌላ ቦታ በማስገባት እና ይዘቱን ወደ ልዩ ስሞቻቸው እና ስልክ ቁጥራቸው በመቀየር ይጠቀማሉ። አንዳንዴ ደግሞ በግልጽ የማይታዩ እነዚህን ዓይነት ማህተሞችንም ይጠቀማሉ።
ህብረተሰቡ ላይ ያለው ተጽእኖ
ባህላዊ ሕክምና በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ ቢውልም በሳይንሳዊ ምርምር በደንብ ያልተደገፉ በመሆናቸው ብዙ ባህላዊ ሕክምናዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ ወይም በትክክል ያልተሞከሩ ናቸው፣ ይህም ወጥነት የጎደለው ዝግጅት እና ሊበከል ይችላል። ተገቢው ደንብ ከሌለ እነዚህ ሕክምናዎች ምን ያህል አስተማማኝ ወይም ውጤታማ እንደሆኑ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ከላይ የተጠቀሰው ክፍተት እያለ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ማጭበርበሮች አስተውለናል። በሳይንስ ያልተፈተሸ ባህላዊ ሕክምና የጤና፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።
በጤና በኩል አንዳንድ እፅዋት ጉበትን፣ ኩላሊትን፣ ልብን ወይም አንጎልን ሊጎዱ ይችላሉ። ብዙ ሰዎች እነዚህ መድሃኒቶች ሙሉ በሙሉ ደህና ናቸው ብለው ስለሚያምኑ በጣም ብዙ ሊወስዱ ወይም ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ከማግኘት ሊዘገዩ ይችላሉ። በማህበራዊ እና ኢኮኖሚ በኩል ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ ለባህላዊ መድሃኒቶች ብዙ ገንዘብ ያጠፋሉ። አንዳንድ ጊዜ ንብረት ይሸጣሉ ወይም ዕዳ ውስጥ ይወድቃሉ፤ ግን ህክምናው አይሰራም። ይህ ደግሞ ድህነትነ ያባብሳል፣ የትምህርት ቤት እና የስራ እጦት እንዲጨምር እና ምርታማነትን እንዲቀንስ ያደርጋል።
መፍትሄዎች በመጀመሪያ በባህላዊ መድኃኒት ጥራት ያለው መረጃ ባለመኖሩ የሀሰት መረጃን በማሰራጨት ወይም ሀሰተኛ መድሀኒቶችን በመሸጥ ህይወትን ለአደጋ እያጋለጠ እና ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን እየበዘበዙ ይገኛሉ።ህብረተሰቡን ለመጠበቅ እነዚህ ግለሰቦች ያልተረጋገጡ ህክምናዎችን ከማስፋፋት ሊታገዱ ይገባል። ከባድ በሆኑ ጉዳዮችም ለብዝበዛቸው እና ለሚያደርሱት ጉዳት ህጋዊ እርምጃ እና ፍትሃዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። በመቀጠልም ስለ ዘመናዊ ህክምና ጥቅም እና ደህንነት የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እና እንዲሁም ሰዎች እንዴት የሀሰት መረጃን እና ማጭበርበርን ለይተው ማወቅ እንደሚችሉ ማስተማር ያስፈልጋል። ማህበረሰቡ ለምን በሳይንስ የተፈተኑ ህክምናዎች ይበልጥ አስተማማኝ እንደሆኑ ግልጽ እና ተደራሽ ትምህርት ያስፈልጋል እና እንዲሁም አሳሳች መረጃነ፣ ያልተረጋገጡ መፍትሄዎችን እና የጤና ማጭበርበርን በመለየት ረገድ ተግባራዊ ክህሎቶችን መማር አለባቸው።
ካልተረጋገጡ መድኃኒቶች መጠንቀቅ አስፈላጊ ቢሆንም ባለ ብዙ አገር በቀል የሕክምና ዕውቀታችንን ችላ ማለት የለብንም። ባህላዊ ልማዶች ለትውልድ ተላልፈዋል እና ዘመናዊ ሳይንስ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ያልዳሰሳቸው ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ሊይዝ ይችላል። እነሱን ውድቅ ከማድረግ ይልቅ እነዚህን መድሃኒቶች በሳይንሳዊ መንገድ የሚያጠኑ፣ ደህንነታቸውን እና ውጤታማነታቸውን የሚፈትሽ ምርምርን መደገፍ አለብን።
ፀሃፊ: ነሞምሳ ዋቅቶሌ