ማቆሚያ ያጡት የኦንላይን ገንዘብ ማጭበርበርያ ስልቶች
በሃገራችን ኢትዮጵያ እየተሰፋፋ ካለው የኢንተርኔት ተደራሽነት አንፃር እና ካለው የወጣቶች የስራ አጥነት ምጣኔ አንፃር በርካታ የኦንላይን ሃሰተኛ የገንዘብ ማጭበርበሪያ መንገዶች ተፈጥረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየተሰራጩ ካሉ የተሳሳተ የገንዘብ ማግኛ መንገዶች መካከል አንዱ 'My Cash Target (MCT)' ነው። ከዚህ በፊት CMV እና 7Eleven በመሳሰሉ ተመሳሳይ ማጭበርበሮች ብዙ ወጣቶች ከፍተኛ ገንዘብ አጥተዋል። የዚህ ጹሐፍ አዘጋጅ CMV በነበረበት ወቅት 21,000 ብር አጥቷል።
MCT የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በመጠቀም ያለ ምንም ክህሎት እና በትንሽ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚገኝ የሚገልጽ የሐሰት መረጃ ነው። ይህ የማጭበርበር አይነት በዋነኝነት በቴሌግራም እና በቲክቶክ ላይ ተሰራጭቷል። MCT በትንሽ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ትርፍ (ለምሳሌ 20 USDT በማስገባት ለአንድ ዶላር ከ300 እስከ 400 ብር በሆነ ስሌት ገንዘብ እንደሚገዙ) እንደዚሁም ሰዎችን በመጋበዝ እስከ 25% ኮሚሽን እንደሚከፍል ይገልፃል።
የMCT የማጭበርበሪያ ዘዴ

የማጭበርበሪያው ዋና ዘዴ የዶላር እጥረት እንዳላቸዉ እና ዶላር የሚያቀርብላቸው ሰዉ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ተጠቃሚዎች ዶላር በዝቅተኛ ዋጋ ማለትም እንደ ባይናንስ ካሉ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያዎች አንድ ዶላር በ160 ብር ገዝተው ወደ MCT እንዲያስገቡና እነሱ ደግሞ በከፍተኛ ዋጋ ማለትም አንድ ዶላሩን ከ300-400 ብር መንዝረው ወደ ባንካቸው እንደሚልኩ ይናገራሉ።
MCT ህጋዊ ስላለመሆኑ የተደረጉ ምርመራዎች
የMCT ድህረ ገፅ የህጋዊነት ምርመራ ውጤት
● በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ፈቃድ ወይም ህጋዊ ምዝገባ የለውም። Email ብለዉ ባስቀመጡት Email Contact ለማድረግ ተሞክሮ ምላሽ አልተገኘም።
● በኦንላይን የምርመራ መሣሪያ በሆነው ScamAdviser ላይ በተደረገ ፍተሻ ድረ-ገጹ (mycashtarget.com) የተሰጠው የደህንነት ውጤት 1/100 ነው።
● የድረ-ገጹ ዕድሜ 4 ወራት ሲሆን ይህም የረዥም ጊዜ ታሪክ የሌለውና ለአጭር ጊዜ የተፈጠረ መሆኑን ያሳያል።

የAI ቪዲዮዎች ትንተና እና መለያ ዘዴዎች:
● በቲክቶክ ላይ የተለጠፉት ቪዲዮዎች በ Artificial Intelligence (AI) የተሰሩ ናቸው።
● ቪዲዮዎቹን የምንለይባቸው መንገዶች:
○ አይን ማርገብገብ (Blinking): የAI ቪዲዮዎች የሰው አይን በተፈጥሮው የሚርገበገብበት ፍጥነት እና ድግግሞሽ የላቸውም።
○ የአካል እና የፊት እንቅስቃሴዎች (Face & Body Proportions): የአካል እና የፊት እንቅስቃሴዎች ተፈጥሯዊ ያልሆኑ፣ ለስላሳ እና የገዘፉ (stiff) ናቸው።
○ የቪዲዮው ርዝመት (Video Length): የAI ቪዲዮዎች ብዙውን ጊዜ አጭር ናቸው።
○ የድምፅ እና የከንፈር እንቅስቃሴ (Lip-sync): የድምፁ እና የከንፈሩ እንቅስቃሴዎች አይጣጣሙም። ለምሳሌ ሴትየዋ "ባዩ" የሚለውን ቃል ስትናገር ከንፈሯ በተፈጥሮ አይንቀሳቀስም። እናም አጥብቃ ነዉ የምታነበዉ።
የፋይናንስ ፍሰት ትንተና:
● ገንዘብ ወደ እነሱ የሚላከው በUSDT (crypto) ነዉ። እናም ይህ ክሪፕቶ ከባንክ ስርዓት ውጭ ስለሆነ ማስተላለፉን ለመከታተልም ሆነ ተመላሽ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው።
የተዛቡ መረጃዎች ትንተና:
● የAI ቪዲዮ ማጭበርበር: በቲክቶክ ላይ @surafielhussen በተባለ አካውንት ከ 97ሺህ በላይ ተከታይ ያለዉ ሲሆን እስከ 27 የሚደርሱ ስለ MCT የሚገልፁ ቪዲዮዎች ተለጥፈዋል። ከነዚህ መካከል አንዱ በ AI የተፈጠረች ሴት ገንዘብ ማግኘትን የምትሰብክ ሲሆን ከ280 ሺህ በላይ እይታ አግኝቷል።
● የቴሌግራም ስርጭት: ከ6,000 በላይ ተከታይ ባለው ግሩፕ https://t.me/MCTAfricaEthiopia003 እና ከ3,000 በላይ ተከታይ ባለው ቻናል ላይ በቀጥታ የድምጽ ስልጠናዎች በመስጠትና የውሸት ገንዘብ ወደ ባንክ የመላክ ቪዲዮዎችን በመልቀቅ ሰዎችን ያታልላሉ። በተለይ ገንዘብ ወደ ባንክ የመላክ ቪዲዮው ገንዘቡ ባንክ ሲገባ የማያሳዩ ሲሆን ገና "pending" ላይ እያለ ገንዘብ እንደተላከ እንዲመስል ያደርጋሉ።

የሰዎች ግንዛቤ እና ተፅዕኖ
ይህ ማጭበርበር በሰዎች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው ለማወቅ ብዬ ለአንድ ሁለት ሚሆኑ ጓደኞቼ እና በMCT የሚባለዉ ግሩፕ ጠይቃለሁ።
የመጀመሪያው ጓደኛዬ "እኔንጃ በ መስሪያ ቤት ሆና ነዉ እያወራች ያለችዉ መስሪያ ቤት ካላቸዉ ደሞ መንግስት ያዉቃቸዋል ንግድ ፈቃድ ይኖራቸዋል ማለት ነዉ ትክክል ይመስላል። ግን አንድ ግራ የሚያጋባ ነገር አለዉ በ ሳምንት እስከ 50000 ሺ ብር እናም ዶላር ከፈለጉ ለምን ከኛ በዉድ ገንዘብ ይገዛሉ ራሳቸዉ እኮ ከነ Bybit or Binance እኮ በርካሽ መግዛት ይችላሉ ትንሽ ግራ ያጋባል ግን ብቻ እንጃ" የሚል ምላሽን አግኝቻለሁ።
ሁለተኛው ጓደኛዬ "አረ ይሄ ነገር ዉሸት ነዉ ሴትዬዋ ራሱ ትክክለኛ ሰዉ አትመስልም እና ደሞ ቅንብር ምስል ነዉ እንጂ ትክክለኛ አይደለም እንዴ ደሞ በ መስሪያ ቤት ሆና ቪድዮዉን እየሰራች እንደሆነ ነዉ ያስመሰሉት። ደሞ በሳምን 50ሺ ለ 1ዶለር ከ300 እስከ 400 ብር እንገዛቹ ምናምን ይላሉ Scam ናቸዉ አረ። እንደዚ ያሉ Scam Website ብዙ ናቸዉ" የሚል ምላሽ ሰጥቶኛል።
ማጠቃለያ እና ምክረ-ሀሳብ
እነዚህ ማጭበርበሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የስራ አጥነት ችግር በመጠቀም ተስፋ ያላቸውን ወጣቶች ገንዘባቸውን እንዲያጡ ያደርጋሉ። እንደ CMV እና 7Eleven ባሉ ማጭበርበሮች ከዚህ በፊት ብዙ ወጣቶች በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ አጥተዋል። በዚያን ጊዜ አጭበርባሪዎቹ 'ሮቦት' ገዝተው እነሱ ትሬዲንግ እንዲያደርጉ ያስችላል በማለት ሰዎችን ያሳምኑ ነበር። ይህ ደግሞ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ መስሎ ስለሚታይ ብዙዎች ተታለዋል።
አንዳንድ ሰዎች ማጭበርበሩን እያወቁ እንኳን 'ቀድመን ከገባን እንጠቀማለን' በሚል አስተሳሰብ ይቀላቀላሉ። በኋላ ላይ ደግሞ ምንም እውቀት የሌላቸውን ሰዎች በመጋበዝ ገንዘብ እንዲያጡ ያደርጋሉ። እነዚህ ማጭበርበሮች ተጠቃሚዎችን ለመያዝ በተደጋጋሚ የሚጠቀሙባቸው የተለመዱ ዘዴዎች አሏቸው።
ሰዎች ድህረ ገፆቹ የማጭበርበሪያ እንደሆኑ በምን ሊለዩ ይችላሉ?
● ያለ ምንም ስራ እና ክህሎት ከፍተኛ ትርፍ የሚሰጥ ቃል መኖሩ።
● አዲስ ሰዎችን ስትጋብዝ የሚሰጥ ትልቅ ኮሚሽን።
● የድርጅቱ እና የባለቤቶቹ ማንነት ግልጽ አለመሆን።
● በAI የተፈጠሩ ወይም ተፈጥሯዊ የማይመስሉ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን ወይም የትላልቅ ድርጅት እና ሎጎ መጠቀም።
ጸሐፊ ሐይሉ ገብሩ