የደራው የሊንክዲን አካውንት ኪራይና የቆዩ የቴሌግራም ግሩፖች ግዢ ጉዳይ
በሃገራችን ኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን መስፋት እና የቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ በበይነ መረብ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና ማጭበርበሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን በርካቶችም ለዚሁ ድርጊት ተጋልጠው በርካታ ቀውሶችን አስተናግደዋል።
አብዛኛው ሰው ገንዘብን በቀላሉ ለማግኘት ከመፈለጉ የተነሳ አጭበርባሪዎች ይህንኑ ድክመት ለተግባራቸው ሲጠቀሙ የሚስተዋል ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሊንክዲን አካውንት ኪራይና የቆዩ የቴሌግራም ግሩፖች ግዢ በይነ መረቡን የተቆጣጠሩ ጉዳዮች ሆነዋል።
የሊንክዲን አካውንት ኪራይና መዘዙ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሊንክዲን አካውንትን በማከራየት በየሳምንቱ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም ደግሞ በቴሌግራም በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል።ይህ ማስታወቂያ 100ሺህ እና ከዛ በላይ ተከታይ ባላቸው የቴሌግራም ቻናሎችም ጭምር በስፋት እየተዋወቀ ይገኛል።
የሊንክዲን አካውንት ማከራየት ማለት ምን ማለት ነው?
የሊንክዲን አካውንትን ማከራየት ሲባል የግል የሊንክዲን አካውንትን መለያን ጨምሮ የይለፍ ቃልና የመግቢያ መረጃን ለሌላ ሰው ወይም ድርጅት ጊዜያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠቀምበት ፈቃድ መስጠትን ያመለክታል። ይህ ተግባርም አከራዩ ወይም የአካውንቱ ባለቤት ገንዘብ እንዲቀበል በማድረግ አካውንቱን የሚጠቀመው ሰው ወይም ድርጅት አካውንቱን በመጠቀም የሚፈልገውን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን እንዲችል ያስችለዋል።
አካውንተን የተከራዩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አካውንቱን ከተከራዩ በኋላ ሊያደርጓቸው ከሚችሏቸው እንቅስቃሴዎች መካከል ከታች የተወሰኑት ተቀምጠዋል።
- አካውንቱን ተጠቅመው መልእክቶችን መላክ፣ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ፣ እንደዚሁም ምርቶችን/አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ ይችላሉ።
- አካውንቱን ተጠቅመው ከሌሎች ተጠቃሚዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ወይም የቢዝነስ እድሎችን መፍጠር ያስስላችዋል።
- ከሌሎች የሊንክዲን ተጠቃሚዎች መረጃን ለመሰብሰብ(Data Mining) ይጠቀሙበታል።
በአጠቃላይ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የግለሰቦችን አካውንት ከተከራዩ በኋላ በአከራዩ አካውንት እና መገለጫ የፈለጉትን ነገር እንዲያደርጉ ዕድል ይሰጣል።
የሊንክዲን አካውንት ለማከራየት የሚጠየቁት መስፈርት ምንድን ነው?
ምንም እንኳን እንከራያለን የሚሉ የተለያዩ ግለሰቦች የተለያዩ መስፈርቶችን ቢያስቀምጡም፤ አብዛኞቹ ገንዘብ የሚገኝበትን ቅድመ ሁኔታዎችን ከተዘረዘሩት ውስጥ መርጠው ያስቀምጣሉ።
የሊንክዲን አካውንትን ለማከራየት ከሚጠይቋቸው መስፈርቶች መካከል:
1/ የሊንክዲን አካውንቱ የተከፈተበት ጊዜ
2/ የጓደኛ/connection ብዛት
3/ የፕሪሚየም አባል መሆን
4/ ሳምንታዊ ጓደኛ ለመጨመር ገደብ የሌለበት
5/ አካውንቱ ቢገደብ/restrict ቢደረግ ባለቤቱ ማስፈታት የሚችል
6/ አካውንቱ መገለጫ ላይ የተቀመጠው የሙያ አይነት
7/ ጠካራ ግንኙነት/Active Engagement
8/ የአካውንቱን መገለጫ እንዲቀየር ፈቃድ መስጠት የሚሉት ይገኙበታል።
ከአሁን በፊት አካውንታቸውን ያከራዩ ሰዎች ምን ይላሉ?
አካውንታቸውን ካከራዩ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው በረከት ቢተው “አንድ ጊዜ ብቻ ነው ብር የላኩልኝ፤ አሁን አካውንቴ ምን ላይ እንደሆነ አላቅም” ይላል።
ሌላኛው አከራይ አብርሃም አሞኘ ደግሞ “ሶስት ጊዜ ብሩን በቴሌብር አስገቡልኝ በአራተኛው አካውንቴ ተዘጋ” በማለት በተጨማሪም በአካውንቱ ምን እንደሚሰራበት በግልጽ እንዳልተነገረውና ለማስታወቂያ/Advertisement ይሆናል በማለት እንዳከራየው ይገልጻል።
አካውንቱን ለመከራየት የሚመጡ ሰዎች የሚከራዩበትን ምክንያት ሲጠየቁም አብዛኞቹ ተከራዮች የሚያቀርቡት ምክንያት እንደ ለፎርኤክስ እና ለስቶክ ማርኬት ማስታወቂያ ላሉ የቢዝነስ ማስታወቂያዎች ብቻ እንደሚጠቀሙበት ይገልፃሉ።
ለምን እንደሚከራዩ ከአንደኛው ተከራይ ጋር የነበረ ጥያቄና መልስ
ግለሰቦቹ አካውንቶቹን የሚከራዩበት ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው ?
ምንም እንኳን መጀመሪያ አካውንቱን ሲከራዩት የሊንክዲን አካውንቱን የሚከራዩት ለቢዝነስ ፕሮሞሽን እንደሆነ ቢገልፁም የመጨረሻ ግቡ ግን አጭበርባሪዎች/ Scammers መረጃ ለማሰባሰብ የሚጠቀሙበት መንገድ ነው።
ሂደቱን ስንመለከትም ማንኛውም ህጋዊ ድርጅት ፕሮሞሽን የሚሰራው የራሱን አካውንት በመጠቀም ወይም ደግሞ በሊንክዲን ላይ በቀጥታ የሚደረግ ማስታወቂያን በመጠቀም ነው። በሊንክዲን ላይ በቀጥታ የሚደረግ ማስታወቂያ ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቅ ይችላል። ስለዚህ እንደአማራጭ ቢጠቀሙ እንኳን ብዙ ተከታዮች ያላቸውን በተለይም በሺዎች የሚቆጠሩ እና ከዚያ በላይ የሆኑ፣ በአንድ የተወሰነ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ከሆኑ (ለምሳሌ: በቴክኖሎጂ፣ በግብይት ወይም በፋይናንስ) እና አካውንቶች ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴ (engagement) ማለትም ፖስቶች የሚያገኙት ላይክ፣ ኮሜንት እና ሼር ብዙ ከሆነ በዚያ ዘርፍ ያሉ ድርጅቶች የምርትና አገልግሎት ማስታወቂያዎቻቸውን ለእነኚህ ተመልካቾች ለማድረስ የሊንክዲን አካውንቶችን ይከራያሉ ወይም የአካውንቱን ባለቤት እንዲያስተዋውቅላቸው ይከፍሉታል።
አጭበርባሪዎች ሰዎች ገንዘባቸውንና የግል መረጃቸውን እንዲሰጧቸው ለማሳመን ቀጥተኛ ያልሆኑና አታላይ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።ስለዚህ አጭበርባሪዎች ህጋዊ በመምሰል እንደ Forex (የውጭ ምንዛሪ) ግብይት፣ የአክሲዮን ማስተዋወቅ ወይም B2B (Business-to-Business) ውድድሮች ያሉ ነገሮችን ይጠቀማሉ። እነዚህ ዘዴዎች ተጠቂዎቻቸውን ለማሳመንና የግል መረጃቸውን ለማግኘት እንደ ሽፋን ያገለግላሉ።
አጭበርባሪዎች ቀጥተኛ ያልሆኑ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ሁለት ማስረጃዎችን አያይዘን ማንሳት እንችላለን። የመጀመሪያው የደንበኞችን ደህንነት የሚጠብቀው የዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት ተቋም የሆነው የፌደራል የንግድ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የማጭበርበር ድርጊቶች አብዛኛውን ጊዜ ቀጥተኛ ባልሆኑ ዘዴዎች ይፈጸማሉ። ለምሳሌ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 የወጣው የኮሚሽኑ ሪፖርት አጭበርባሪዎች የሌላ ሰው ማንነት በመጠቀም (impersonation scams) የፈጸሟቸው ማጭበርበሮች ተጎጂዎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር እንዲያጡ አድርጓል።
ሁለተኛው በሳይኮሎጂ እና በሶሺዮሎጂ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አጭበርባሪዎች የሚሳካላቸው የሰዎችን እምነትና አስተሳሰብ በመጠቀም ነው። የውሸት ሁኔታዎችን በመፍጠር ጥያቄያቸው ሕጋዊ እንዲመስል ያደርጋሉ። ለምሳሌ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ኢንቨስትመንት (እንደ ፎሬክስ ወይም የአክሲዮን ግብይት) በማቅረብ መጀመሪያ ላይ ግንኙነት ይፈጥራሉ።
አጭበርባሪዎች የውሸት ሥራዎቻቸውን ሕጋዊ ንግድ አስመስለው ሲያቀርቡ የዩናይትድ ስቴትስ የሸቀጦች የወደፊት ንግድ ኮሚሽን (CFTC) እና የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (FINRA) በተጭበረበሩ የፎሬክስ እና የክሪፕቶ ምንዛሪ ኢንቨስትመንት እቅዶች ላይ ብዙ ማስጠንቀቂያዎችን አውጥተዋል። አጭበርባሪዎች የውሸት የግብይት ድረ-ገጾችን ወይም መድረኮችን በመፍጠር ለተጎጂዎች የውሸት ትርፍ ያሳያሉ። ይህ ዘዴ ተጎጂዎቹ የበለጠ ገንዘብ እንዲያስገቡ ያበረታታል። ለምሳሌ፣ እ.ኤ.አ. በ2022 CFTC በDigital Commodity Trading Group በሚባል ኩባንያ ላይ ክስ አቅርቧል፤ ይህ ኩባንያ ትርፍ እንደሚያስገኝ ቃል የገባ፣ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ የማጭበርበር እቅድ የነበረው ነበር።
ሌላኛው ዘዴ የተለዩ ኢላማዎችን በመያዝ ታዋቂ የንግድ አጋር ወይም አቅራቢ አስመስለው የኩባንያ ሰራተኞችን ገንዘብ ወይም ሚስጥራዊ መረጃ እንዲልኩ ያታልላሉ። ይህ ደግሞ "B2B" የሚለውን አውድ ተጠቅሞ ማጭበርበርን ያሳያል።
የሊንክዲን የአጠቃቀም ስምምነት የማጭበርበር እና ሐቀኝነት የጎደለው ተግባርን የአካውንት ኪራይን ጨምሮ በግልጽ ይከለክላል። የመተግበሪያው ደንቦች "ማንነትዎን ማጭበርበር፣ የተሳሳተ ይዘት ማተም ወይም የውሸት መገለጫዎችን መፍጠር የለብዎትም..." እና "አገልግሎቶቻችንን ማንንም ለማጭበርበር ወይም ለማሳሳት መጠቀም የለብዎትም" ይላል።
ሕጋዊ ኩባንያዎች በሊንክዲን ላይ ቅጥር፣ ግብይት ወይም ግንኙነት ለመፍጠር ሲጠቀሙ እነዚህን መርሆች ማክበር አለባቸው። እነዚህን ደንቦች ማፍረስ የአንድ ኩባንያ ገጽ እንዲዘጋ ወይም የሰራተኞቹ መለያዎች እንዲታገዱ ሊያደርግ ይችላል።
ብዙ ሕጋዊ ኩባንያዎች ትክክለኛነታቸውን ለማሳየት በሊንክዲን ላይ የማረጋገጫ ሂደት ውስጥ ያልፋሉ። ለምሳሌ፣ የሊንክዲን "Official Company" (ኦፊሴላዊ ኩባንያ) ምልክት ተጠቃሚዎች ሕጋዊ ንግድን ከተጭበረበረው እንዲለዩ ይረዳቸዋል። አጭበርባሪዎች ግን የውሸት ወይም ያልተረጋገጡ መለያዎችን ይጠቀማሉ።
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስለ ጉዳዩ ምን ይላሉ?
አጭበርባሪዎች መረጃን የሚሰበስቡት የኤአይ ሞዴል ለማሰልጠን እንደሚጠቀሙበት ሲገለፅ የኤአይ መምህሩ አቶ አብነት ዓለሙ “ሃሰተኛ የስራ ማስታውቂያዎችን በሊንክዲን በመልቀቅ የሚያመለክቱትን ግለሰቦች የእያንዳንዳቸውን መረጃዎች እንደዋነኛ የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ለስራቸው የሚያግዝ የኤአይ ሞዴል በማሰልጠን ለማጭበርበር ይጠቀሙበታል” በማለት ያብራራል፡፡
የቀድሞው የሳይበር ባለሙያ አቶ ካሳሁን “Login credential (የይለፍ ቃል) የአንድ ሰው ማንነት ነው። አንዴ ሲያጋሩት የግል መሆን ያቆማል፤ በዚህም ማንኛውም አጠራጣሪ እንቅስቃሴ በዚህ ስም የተፈጸመ ተደርጎ ይወሰዳል። ፓስዎርዶች/የይለፍ ቃሎች የጥርስ ብሩሽ ማለት ናቸው፤ አያጋሯቸው፣ ደጋግመው አይጠቀሙባቸው ወይም በመደበኛነት ይቀይሯቸው የሚባለው የማንነት ቁጥጥርን እንደ ማጣት ስለሆኑ ነው” ይላሉ።
ሊንክዲን አካውንት ማከራየት እና ወንጀል
ሊንክዲን አካውንት ማከራየት እና ወንጀል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው የሆነ ግለሰብ ወይም ቡድን የሌላ ሰው ሊንክዲን መለያ በገንዘብ ወይም በሌላ መንገድ ተከራይቶ ለተለያዩ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች መጠቀምን ነው። እንደነዚህ ያሉ ወንጀሎች በሊንክዲን መድረክ ላይ በተለይ በቅርብ ዓመታት መከሰታቸው ተመዝግቧል።
በታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ከሊንክዲን ጋር ተያያዥነት ያላቸው የተወሰኑ የሳይበር ወንጀል ምሳሌዎች እንመልከት።
1. ማጭበርበር በሊንክዲን (Phishing Scams) ፡ የሀሰት ሥራ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ፣ የሐሰት ኩባንያዎችን ወይም አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ።
- በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ደግሞ በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ ውስጥ በስፋት ተስተውሏል።
- ከ2010ዎቹ ጀምሮ የሊንክዲን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ተስፋፍቷል።
- ይህ ወንጀል የተፈጸመው በሳይበር ወንጀለኞች፣ በተለይ በተደራጀ የሳይበር ወንጀል ቡድኖች፣ እንደ ሩሲያና ቻይና ባሉ አገሮች ተመዝግበው በነበሩ ሃከሮች ነው።
- ወንጀሉን የሚፈጽሙትም የግል መረጃዎችን (እንደ ኢሜይል፣ ፓስዎርድ፣ የሥራ ታሪክ) ለመስረቅ፣ የሐሰት ሥራ ማስታወቂያዎችን ለማሰራጨት፣ ወይም ለፋይናንሺያል ማጭበርበሪያ መረጃ ለመሰብሰብ ነበር።
- ለምሳሌ በ2016 የሊንክዲን የውሂብ መጥፋት(data breach) ከተከሰተ በኋላ ከ117 ሚሊዮን በላይ የተጠቃሚ መለያዎች መረጃ ተሰርቋል፣ ይህም በወንጀለኞች ለማጭበርበር እና ለማንነት መስረቅ ተጠቅመውበታል።
2. የሐሰት መለያዎች መፍጠር እና አጠቃቀም
- በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ከ2015 እስከ አሁን የተለያዩ የሊንክዲን ሀሰተኛ መለያዎች ተከፍተዋል።
- ይህ የሚከናወነውም በተመመሳሳይ መልኩ በግለሰቦች ወይም በተደራጁ የሳይበር ወንጀል ቡድኖች ነው።
- የሐሰት መለያዎችን በመፍጠር ወይም ተከራይተው የተገኙ መለያዎችን በመጠቀም ወንጀለኞች የሥራ ማስታወቂያዎችን፣ የኢንቨስትመንት ማጭበርበሪያዎችን፣ ወይም የማልዌር ሊንኮችን ያሰራጫሉ።
-ለምሳሌ በ2020 ዓ.ም በሊንክዲን ላይ የሐሰት የሥራ ማስታወቂያዎች በስፋት ሲስተዋል በተለይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሰዎች የሥራ ዕድል ሲፈልጉ ስለነበር እነዚህ ማስታወቂያዎች ተጠቃሚዎችን ወደ የሐሰት ድረ-ገፆች በመምራት የግል መረጃዎችን ይሰርቁ ነበር። ይህን ተከትሎም FBI በሊንክድኢን በኩል የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ግልጽ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር።
እነዚህ ማጭበርበሮች ብዙ ጊዜ ከሌሎች የተወሰዱ ወይም በኪራይ ከተያዙ አካውንቶች የሚመነጩ ሲሆን ተጎጂዎችን የቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ ወይም በሀሰተኛ ቼክ ፕሮግራሞች እንዲሳተፉ በማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እና የማንነት ስርቆት እንዲደርስባቸው አድርገዋል። ከFBI በተጨማሪ ሊንክድኢን እና ወላጅ ኩባንያው ማይክሮሶፍት በአካውንት የአጠቃቀም ስምምነታቸው መሰረት አካውንቶችን መግዛት፣ መሸጥ ወይም ማከራየት እንደማይፈቀድ በግልጽ ሲያስቀምጡ ይህን የሚጥሱ አካውንቶችንም በቋሚነት እንዲታገዱ እያደረጉ ይገኛሉ።
- በሌላ ማሳያ ወንጀለኞች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን ለመስረቅ የሊንክድኢን ፕሮፋይሎችን በኪራይ እንደተጠቀሙ ቢቢሲ በጥቅምት 2021 ባወጣው ዜና ላይ ገልጿል። የቢቢሲ ምርመራ እንዳሳየው ዓለም አቀፍ አጭበርባሪዎች የሰዎች የሊንክድኢን ፕሮፋይሎችን የሚከራዩበት ጥቁር ገበያ ተፈጥሯል። እነዚህ ወንጀለኞች በባለሙያዎች ማንነት እየተጠቀሙ ከተጎጂዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ገንዘባቸውን ወደ ሀሰተኛ የክሪፕቶከረንሲ ኢንቨስትመንት እንዲያስገቡ በማታለል ገንዘባቸውን ዘርፈዋል። አንድ እንግሊዛዊ ተጎጂ ከ100,000 ፓውንድ በላይ እንዳጣ ተናግሯል። እነዚህ አካውንቶች ብዙውን ጊዜ ከትክክለኛ ባለቤቶቻቸው በየወሩ ክፍያ እየተከፈላቸው የሚከራዩ ሲሆን ይህ አዲስ የኦንላይን ማጭበርበር ዘመናዊ ዘዴ መሆኑን አሳይቷል።
- ሶስተኛው ምሳሌ በ2022 ዓ.ም. የሳይበር ደህንነት ተመራማሪዎች "SolarWinds" እና "Microsoft Exchange" በሚባሉ የሳይበር ጥቃቶች ላይ የሊንክዲን አካውንቶችን እንዴት እንደተጠቀሙባቸው አጋልጠዋል። በዚህ ጥቃት የሊንክዲን አካውንት የተከራዩ የሳይበር ወንጀለኞች እንደ ትክክለኛ የሰው ኃይል ባለሙያዎች (HR professionals) በመሆን የውሸት የስራ ቅናሾችን የሚያሳይ ዶክመንት አዘጋጅተዋል። ከዚያም ይህን ዶክመንት ለተለያዩ ኩባንያ ሰራተኞች በሊንክዲን መልእክት ልከዋል። ሰራተኞቹም መልእክቱን በማመን የዶክመንት ፋይሉን ሲከፍቱ በውስጡ የነበረው አደገኛ ማልዌር ኮምፒውተራቸው ውስጥ የነበሩ መረጃዎችንም ሰርቋል።
በአጠቃላይ ወንጀለኞች የተከራዩትን መለያውን በመጠቀም እራሳችውን በሌላ ማንነት ለመደበቅ፣ የግል መረጃዎችን ለመስረቅ የሐሰት መልእክቶችን ለመላክና ተንኮል አዘል ሶፍትዌሮችን ለማሰራጨት ተጠቅመውበታል።
የሊንክዲን አካውንት ማከራየት አደጋዎች
ሊንክዲን አካውንት ማከራየት ገቢ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ቢሆንም ከፍተኛ አደጋዎች አሉት። ሊከሰቱ የሚችሉት ችግሮችም የሚከተሉት ናቸው።
● አካውንትን ሲያከራዩ የይለፍ ቃልን ለአከራዩ መስጠት ግዴታ ሊሆን ይችላል። ይህም የግል መረጃዎችን፣ ግንኙነቶችን እና ሙያዊ ምስጢሮችን አደጋ ላይ ይጥላል። ተከራዩ የይለፍ ቃል/password ቀይሮ አካውንቱን ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠረው ወይም ሊሰርቀው ይችላል።
● ሊንክዲን የአካውንት ኪራይን በይፋ አይደግፍም። ስለዚህ ሊንክዲን የአካውንት ኪራይን እንዳወቀ ህጎቹን እንደጣሱ በመቁጠር አካውንቱን ሊዘጋው ወይም ሊያግደው ይችላል። በዚህ ምክንያት ለዓመታት የተገነባው ግንኙነት ሊጠፋ ይችላል።
● አካውንቱን የተከራየው ሰው የአከራዩን ስም በመጠቀም ከአከራዩ እምነት እና ሙያዊ ስነምግባር ውጪ የሆኑ ነገሮችን ሊያሰራጭ ይችላል። ይህ ደግሞ በሙያዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ከዚህም አልፎ በአካውንቱ ስም ወንጀል ሰርቶ ተጠያቂ ያደርጋል።
እንደዚህ ያሉ ወንጀሎች ለምን በሊንክዲን ይከሰታሉ?
- ሊንክዲን በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት መድረክ ሲሆን ይህም ለሳይበር ወንጀለኞች ማራኪ ኢላማ ያደርገዋል።
- ሊንክዲን በተለምዶ ሙያዊ መድረክ ተደርጎ ስለሚታይና ከሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በበለጠ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተዐማኒ ስለሆነ ለማጭበርበር እድል ይሰጣል።
- የሐሰት መለያዎችን በመጠቀም ጰየተጠቃሚዎችን መረጃ በመሸጥ ወይም በማጭበርበር ወንጀሎች ከፍተኛ ገንዘብ እእዲያገኙ ያስችላል።
ደህንነታቸው የተጠበቁ አማራጭ የገቢ መንገዶች
የሊንክዲን አካውንትን ለኪራይ ከማጋለጥ ይልቅ በይበልጥ አስተማማኝ በሆኑ መንገዶች ገቢ ማግኘት ይቻላል።
● ተባባሪ (Affiliate) ግብይት: ከአንድ ኩባንያ ጋር በመተባበር ምርቱን ወይም አገልግሎቱን በአካውንት ላይ ማስተዋወቅና ከተሸጠው ሽያጭ ኮሚሽን ማግኘት ይቻላል። ይህ ዘዴ የአካውንትን ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ ለማስተዳደር ይረዳል።
● የስፖንሰር ፖስቶች: አንድ ድርጅት በሊንክዲን አካውንት ላይ አንድ ፖስት እንዲለቅ ሲጠይቅ ፖስቱን ባለቤቱ እንዲለቅና የሚፈልጉትን መረጃ ሲያስተላልፍላቸው ክፍያ ሊሰጡት ይችላሉ።
● የምርት ግምገማ (Product Review): በሙያ ላይ የተመሰረተ ምርት ወይም አገልግሎት ካለ በአካውንቱ ላይ ግምገማ በማድረግና አስተያየት በመስጠት ከኩባንያዎች ገቢ ማግኘት ይቻላል።
የቆዩ የቴሌግራም ግሩፖች ሽያጭ ጉዳይስ?
እንደ ሊንክዲን አካውንት ሁሉ አሁን አሁን በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም በቴሌግራም የቆዩ የቴሌግሪም ግሩፖች ግዢ እና ሽያጭ ደርቷል።
ከአሁን በፊት የቆዩ የቴሌግራም ግሩፖቹን የሸጠው ሙሉሰው ጉደታ "ለፕሮሞሽን ነው የምፈልገው ስላለኝ ባለቤትነቱን ለገዢው ካስተላለፍኩ በኋላ የተስማማንበትን ዋጋ በሞባይል ባንኪንግ ላከልኝ። ቻናሎችን ከሸጥኩ በኋላ በየጊዜው የተለያዩ የማላቃቸው ሰዎች ሀይ ይሉኛል አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ገንዘብ አግኝ የሚል የማይጠቅም ሊንክ ይልኩልኛል" ይላል።
ስለዚህ ምንም እንኳን የቆዩ የቴሌግራም ግሩፖችን በመሸጥ ውስን ገንዘብ የሚገኝ ቢሆንም በውስጡ ተጠቃሚዎችን አደጋ ላይ የሚጥሉ ለአላስፈላጊ ሊንኮችና ለአጭበርባሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ሆነዋል። ሻጩ ባለቤትነትን ብቻ እያስተላለፍኩ ነው ብሎ ቢያስብም መሸጡ አደጋም አለው።
1. የህግ አደጋዎች (Legal Risks)
አዲሱ ባለቤት ግሩፑን ለማጭበርበር ወይም ህገወጥ ተግባራትን ለመፈፀም ከተጠቀመበት መርማሪዎች በመጀመሪያ ሻጩን ተጠያቂ ሊያደርጉ ይችላሉ።
2. የስም መበላሸት (Reputation Damage)
በግሩፑ ውስጥ የነበሩ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦች፣ ወይም ተከታዮች ከዝውውሩ በኋላ ሻጩን ከማጭበርበር ጋር ሊያገናኙት ይችላሉ።
3. የደህንነት አደጋዎች (Security Risks)
ሻጩ ማንኛውንም የአድሚን መዳረሻ (admin access) ወይም የአካውንት ትስስር (account links) ከያዘ አዲሱ ባለቤት ሊጠቀምበት የግል መረጃን ለመስረቅ፣ በሌላ ስም ተንኮል አዘል ማገናኛዎችን (malicious links) ለመላክ ሊጠቀምበት ይችላል።
4. የገንዘብ አደጋዎች (Financial Risks)
ክፍያውን አስቀድመህ ከተቀበልክ እና ግብይቱ አስተማማኝ ባልሆኑ መንገዶች (ክሪፕቶ፣ ቀጥታ የባንክ ዝውውር) ከተፈጸመ፣ የክፍያ ተመላሽ (chargebacks) ወይም ውዝግብ ሊኖር ይችላል። ገዢው አጭበርባሪ ከሆነ በኋላ ላይ አጭበርብረኸኛል ብሎ ገንዘቡን መልስልኝ ሊል ይችላል።
5. የስነምግባር አደጋዎች (Ethical Risks)
ገዢውን ሳትመረምር ግሩፕ መሸጥ በተዘዋዋሪ ማጭበርበርን የተሳሳተ መረጃን ወይም ትንኮሳን ሊያስከትል ይችላል። ግሩፑ አላግባብ ጥቅም ላይ ከዋለ እንደተባባሪ ሊቆጠር ይችላል።
6. የስርዓተ ፖሊሲ አደጋዎች (Platform Policy Risks)
የቴሌግራም የአገልግሎት ውል (Terms of Service) ግሩፖችን መሸጥን ወይም ማስተላለፍን እንደሊንክዲን በይፋ አይደግፍም። ደንቦችን መጣስ አካውንት እንዲታገድ ሊያስደርግ ይችላል።
ያልተሳኩ ቃለ መጠይቆች
ከአምስት በላይ ቃለ መጠይቆች አልተሳኩም። ምክንያቶቹም ለርዕሱ አዲስ መሆንና የስራ ብዛት ነበሩ። ከተጠያቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ የቴክኖሎጂ መምህራንና ባለሙያዎች ነበሩ።
ጸሐፊ፡ ደሳለው ጋሻየ