በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልድያ ቅርንጫፍን በተመለከተ የተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ
ወልድያ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው የሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ ወልድያ ናት። በቅርቡ በወልድያ ከተማ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት ላይ ውሏል በተባለ ደረሰኝ ዙሪያ የተሳሳተ መረጃ ተሰራጭቷል።

ከላይ በምስሉ እንደሚታየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦሮምኛ ቋንቋ መጀመሪያ ላይ አስቀምጦ በሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋን በማስቀመጥ ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት በዚህ ደረሰኝ አማካኝነት እንዲያገኙ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ደረሰኝም ከአማሪ ክልል ወልድያ ከተማ ከሚገኙ የፌስቡክ ገፅ ተከታዮቼ የተላከልኝ ነው በሚል በርካታ ተከታዮች ያሉት አሳየ ደርቤ የተባለ አክቲቪስት ደረሰኙን ለተከታዮቹ አጋርቷል። አክቲቪስቱ ከ229 ሺህ በላይ ተከታዮች ሲኖሩት ያጋራው የተሳሳተ መረጃ መረጃው ሲዘጋጅ ከ1800 በላይ ላይክ፣ 611 ኮሜንቶች ሲሰጡ 92 ሰዎች ፅሁፉን አጋርተውታል።
ይሀንን ፎቶ ሌሎች በርካታ ተጠቃሚዎች ያሏቸው ተጠቃሚዎችም ባለማወቅ ሲያጋሩት በቦታው በመገኘት በተደረገው ማጣራት በወልድያ ከተማ አገልግሎት ላይ ውለዋል የተባሉ ደረሰኞች ዘገባ የተሳሳተ መሆኑ ተረጋግጧል። በወልድያ ከተማ በሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ በመገኘት በተመለከትነው መሰረትም ባንኩ በዘገባው የተሰራጨውን ደረሰኝ እየተጠቀመ አይደለም።
በወልድያ ከተማ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት ላይ ዋሉ የተባሉ ደረሰኞች ከየት መጡ?
የእነዚህን ደረሰኞች ትክክለኛ መምጫ ለማረጋገጥ ወደ ባህርዳር ከተማ ወደሚገኝ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በማምራት በተደረገ ማጣራት ደረሰኞቹ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ያሉት በርካታ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሉበት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚሴ መሆኑ ታውቋል።