የትርፍ አንጀት በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ላይ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች
ኢትዮጵያ ውስጥ የትርፍ አንጀት በሽታ መተላለፊያ መንገዶችን በተሳሳተ መንገድ ተረድቶ ከምግብ በኋላ ገላን መታጠብ እና መሮጥ ወይም መንቀሳቀስ ትርፍ አንጀት በሽታ ያስከትላል የሚል ትክክለኛ ያልሆነ የተሳሳተ መረጃ ማህበረሰብ ውስጥ በስፋት ተስፋፍቶ ይገኛል። እንደዚህ አይነት የተሳሳተ መረጃ በማህበረሰብ ውስጥ ቢኖርም ግን ይህ መረጃ በህክምና እና በሳይንሳዊ ምንጮች የማይደገፍ የተሳሳተ መረጃ ነው።
በመረጃው ላይ የህክምና ባለሙያ ምን ይላሉ?
ይህንን ሃሰተኛ አባባል በተመለከተ በዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሙሀመድ አድን ሃሳባቸውን አጋርተዋል። ዶ/ር ሙሀመድ አድን እንደገለጹት ከምግብ በኋላ በቀጥታ ጥብቅ የሆነ የአካል ብቃት ሥራ ማለትም መሮጥ ማድረግ ለሁሉም ሰው ጤናማ አይደለም። ይህ ለሆድ ቁርሾ cramps ወይም ለመጨናነቅ discomfort ሊያደርግ ይችላል፣ ነገር ግን ትርፍ አንጀት አያስከትልም። ከምግብ በኋላ ቀስ በቀስ መሄድ ይመከራል ብለዋል።
እንደ ባለሙያው አስተያየት የትርፍ አንጀታችን የውስጠኛው ክፍል በሚዘጋበት ወቅት የትርፍ አንጀት በሽታ ይከሰታል። ትርፍ አንጀት በተለያዩ ኢንፌክሽኖች ምክንያት ለምሳሌ:- እንደ ቫይረስ፣ ባክቴሪያ ወይም በምግብ መፍጫ ቱቦዎች ውስጥ በሚገኙ ጥገኛ ተህዋሲያን (Parasites) ሊከሰት ይችላል ብለዋል። ትልቁ አንጀትን እና ትርፍ አንጀትን የሚያገናኘው ቱቦ በሰገራ በሚደፈንበት ወይም በሚዘጋበት ጊዜ የትርፍ አንጀት በሽታ (Appendicitis) ሊከሰት ይችላል።ነገር ግን ትርፍ አንጀት በሽታ ከምግብ በኋላ ገላን በመታጠብ እና ምግብ ከበላን በኋላ በመንቀሳቀስ ወይም በመሮጥ የሚፈጠር ነገር እንዳልሆነ ገልፀዋል።
ለትርፍ አንጀት ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?
በአብዛኛው የትርፍ አንጀት በሽታ ከ 10 - 30 ዓመት እድሜ ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ይከሰታል። በተለይ ወንድ ከሆኑ በቤተሰብ ውስጥ የትርፍ አንጀት በሽታ የያዘው ሰው ካለ በበሽታው የመያዝን አደጋ ከፍ ያደርገዋል። ህጻናት ሲስቲክ ፊብሮሲስ ( Cystic Fibrosis) ካለባቸው በትርፍ አንጀት የመያዝ እድላቸውን ይጨምራል።
የትርፍ አንጀት ሕመም ምልክቶችና ምክረ ሃሳብ
ከሆድ ጠርዝ ላይ ጀምሮ ወደ ታችኛው ቀኝ የሆድ ክፍል ይሄዳል። እንዲሁም በታችኛው የሆድ በቀኝ በኩል ሊጀምር ይችላል። በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ፣ በጥልቀት ሲተነፍሱ፣ ሲነኩት (ሲነካ) እና ሲያስሉ ወይም ሲያስነጥሱ የከፋ የህመም ስሜት ሊሰማዎት ይችላል። የትርፍ አንጀት በፍጹም የሚከላከል መንገድ ባይኖርም የሚረዱ ዘዴዎች አሉ። ፍራፍራዎች እና አትክልቶች ያሉበት አመጋገብ መብላት።በቂ ውሃ መጠጣት፣የታሸገ ምግቦችን በትንሹ መጠቀም ከሚረዱ መንገዶች ጥቂቶቹ ናቸው።
ዶ/ር ሙሀመድ አድን እንደገለጹት ት ርፍ አንጀት በሽታ የሚፈጠረው በአንጀት መዝጋትና በባክቴሪያ ኢንፌክሽን ምክንያት ነው። ስለዚህ ማህበረሰብ ማወቅ የሚገባው ነገር የጤና ሚኒስቴር፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የህክምና ባለሙያዎች በቀጥታ የሚሰጡትን መረጃ ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ፀሃፊ: አብዱ አሊ