post-thumb

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በግብፅ መገናኛ ብዙሃን ሲሰራጩ የከረሙ የተሳሳቱ ዘገባዎች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከወርሃ መጋቢት 2003 ጀምሮ ሲገነባ  ኢትዮጵያውያን የይቻላልን መንፈስ ያሳኩበትና በ3000 ዓመታት የሀገርነት ጉዞ ውስጥ ከተከወኑ ግዙፍ አሻራዎቻቸው ውስጥም  ተጠቃሹ ነው። ይህ ግድብ ለዘመናት በትውልድ ውስጥ ለተፈጠር ቁጭት መልስ ሰጠ እና የበይ ተመልካችነት ታሪክን ቀይሮ ግንድ ይዞ ዟሪውን ወንዝ ማደሪያ የሰጠም ነው።ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን የደረሠበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ግን የተለያዩ ሸፍጦች ተፈጽመዋል። የሃሰት ወሬዎች ተፈጥረው የኢትዮጵያውያንን የትብብር መንፈስ ለማዳከምም ታልሞ ተሠርቷል።ዳሩ ግድቡ መጠናቀቁ ባይቀርም  የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የራሳቸውን ህዝብ ለማረጋጋት በአንጻራዊነት ኢትዮጵያውያንን ለማስደንገጥ ብሎም የተቀረውን ዓለምን ለማሳሳት በመገናኛ ብሀዙሃኖቻቸው ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል።

ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት አንዷ ግብጽ እንደ ሀገር አርማ በሚታይበት አሃራም ኦንላይን በተሰኘው የብዙሃን መገናኛዋ ብቻ ይህ ጽሁፍ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከ 460 ጊዜ በላይ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዘገባዎች መሠራቱ ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሠጡበት ማሳያ አድርገን ልንወስድ እንችላለን።ጠብታ ውሃ ከፍላጎታችን ሊቀንስብን አይገባም ፣ የቀደሙ ስምምነቶች ሊከበሩ ይገባል ፣ በአባይ ወንዝ ላይ የተናጠል የልማት ዕቅዶች ተቀባይነት የላቸውም እና የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጽያ በአባይ ወንዝ ላይ እያካሄደች ያለውን የግድብ ግንባታ ይምከርበት የሚሉት አንኳር ጉዳዮች ደግሞ በታችኛው የተፋሠሡ ሀገራት ማለትም በግብጽና  ሱዳን መገናኛ ብዙሃን በስፋት ትኩረት ያገኙ ናቸው።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት በሀገር ውስጥ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ሀሠተኛ መረጃዎች መካከል ግድቡ በሚሰራበት ስፍራ ከወገብ በላይ ሰው ከወገብ በታች ደግሞ እባብ የሆነች ፍጥረት ተገኘች በሚል ባለቤቱ በውል የማይታወቅ ተንቀሳቃሽ ምስል ተጠቃሹ ነው።ይህ ከተፈጥሮ ጋር የሚጻረር ሃሰተኛ መረጃ ምንም እንኳን ሰዎች ባለማወቅ "ግድቡ እንዳይሰራ የግብጽ ሴራና የሱዳን መተት ነው "በሚል ቢቀባበሉትም በግድቡ ግንባታ ሂደት የራሱ የሆነ ተጽዕኖ የማሳደር ዕድል ግን ነበረው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግንባታ ሂደቱ ከፍተኛ የሰው ሃይል ይፈልግ የነበረ ሲሆን ይህ መረጃ ኢትዮጵያውያን ካላቸው ሃይማኖታዊ እሳቤ አንጻር ስነ ልቦናዊ ጫና በማሳደር ወደ ስፍራው ለስራ እንዳይሄዱ ፍራቻን የሚፈጥር መረጃም ነበር።እዚህ ላይ ለስራ ወደ ጉባ ለመሄድ ካቀደ በኋላ ሀሳቡን የሰረዘውን የጎንደር ነዋሪውን አለልኝ አማረ በአስረጅነት መጥቀስም ይቻላል።

በሌላ በኩል ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ሂደት ዓለምአቀፍ ህጎችንና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ጥሳለች የሚለው ጉዳይ ተደጋግሞ ሲነሳ አስተውለናል። የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ከመጣስ ጋር በተያያዘ ከጻፉ ሰዎች ደግሞ የካይሮ ዩንቨርስቲ የጂኦሎጂ ፕሮፌሰሩ አባስ ሻራኪ አንዱ ናቸው።

አባስ ሻራኪ እንደ እኤአ በ2022 በፌስቡክ ገጻቸው በጻፉት ጽሁፋቸው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር የተፈራረመቻቸውን የ1891 ፣ 1902፣1906ና 1925 ስምምነቶች ጥሳለች ሲሉ ከሰዋል። ይሁን እንጂ ፕሮፌሰሩ ይህንን ብለው ኢትዮጵያን ቢከሱም ከተጠቀሱት አራት ስምምነቶች ኢትዮጵያ በ3 ቱ አልተገኘችም።ከዚህም ባሻገር በእነዚህ ስምምነቶች የመፈረም ሂደት ውስጥ ግብጽ ራሷ ነጻ ሀገር ያልነበረችና በቀኝ ገዥዎች የተፈጸመ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል። 'Major historical agreements of the Nile Basin' በሚል መቅደላዊት መሳይ weaspire.inf[1]  ላይ ለንባብ ያበቁት ጽሁፍ ፕሮፌሰር አባስ ሀሰተኛ መረጃ ለማሰራጨታቸው መረጃ አድርገን ልናቀርብም እንችላለን።እንደ መቅደላዊት በ1891 የተፈጸመው ስምምነት በጣሊያንና በእንግሊዝ መካከል ሲሆን የስምምነቱ አንኳር ሀሳብም በተከዜ ወንዝ ላይ ጣሊያን ለመስኖ አገልግሎት ግድብ እንዳትገነባ የሚያስገድድ ነበር።

በፕሮፌሰር አባስ ሻራኪ በኢትዮጵያና በግብጽ ተፈርመዋል የተባሉት የ1906 ና የ1925 ስምምነቶችም ሁለቱ ሀገራት በቀጥታ የፈጸሟቸው ሳይሆን በእንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ ና ጣሊያን የተፈጸሙ ናቸው።እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት አስገብተን በፕሮፌሰሩ የቀረበውን ይህን ሀሰተኛ ጽሁፍ ስናጤን ፣ የኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከህግ አኳያ ተቀባይነት የሌለው ነው የሚለውን ስሁት ትርክት በማስተላለፍ ግብጻውያን ብሎም የተቀረው ዓለም ለኢትዮጵያውያን የግድብ ግንባታ በጎ እይታ እንዳይኖረው ለማድረግ ያለመ መሆኑን እንረዳለን። ሌላኛው በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከተሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል በማህበራዊ ትስስር ገጾችና በግብጽ የብዙሃን መገናኛዎች ሲዟዟር የነበረው በታላቁ ህዳሴ ግድብ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ የሚለው ጉዳይ ተጠቃሹ ነው።በዚህ ጉዳይ ሃሰተኛ መረጃ ካሰራጩ መገናኛ ብዙሃን መካከል ደግሞ የግብጹ' egypt independent' አንዱ ነው። ምንም እንኳን ይህን ዓመት ጨምሮ በሌሎችም ጊዜያት በኢትዮጵያ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰትም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግን የመሬት መንቀጥቀጥ በቅርብ ጊዜያት አልተከሰተም። የኢትዮጵያ ጂኦሎጅካል ኢንስቲቲዩትም ጉዳዩ የፈጠራ ወሬ መሆኑን ከመረጃው መሠራጨት በኋላ በሠጠው ምላሽ አረጋግጧል።

ሌላኛው ከተፈጥሮ አደጋ ጋር በማያያዝ በግብጻውያን የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲሰራጭ የነበረው ጉዳይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተያዘው ውሃ ወደ መሬት በመስረጉ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ተሰነጠቀ የሚለው ሀሰተኛ መረጃ ይጠቀሳል።

በእርግጥ በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ በአንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መሰንጠቅ ማጋጠሙ ባይካድም መሬቱ የተሰነጠቀበት ምክንያት ግን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ ጋር የሚያያዝ አይደለም።በጉዳዩ ላይ ጥናቶችን የሰሩ አካላት እንደሚሉት ለስምጥ ሸለቆ አካባቢ የመሬት መሰንጠቅ ዓይነተኛ ምክንያት በየዓመቱ መንሸራተት የሚታይባቸው የኑቢያና የሶማሊያ ፕሌቶች እንቅስቃሴ ነው።ከዚህ ባሻገርም የእሳተ ጎመራና  የመሬት መንቀጥቀጥ ለሁነቱ መፈጠር በመንስዔነት ሲጠቀሱ የውሃ ወደ መሬት መስረግ ግን ለመሬት መሰንጠቁ ምክንያት ነው ተብሎ በጥናቶች አልተገለጸም።[2]  

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ በሚጠቀሙ ግብጻውያን ከተፈበረኩ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል የጣና ሃይቅ የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ የታላቁ የህዳሴ ግድብም የመፍረስ አደጋ ተጋረጠበት የሚለው ይገኝበታል።

በዚህ ጽሁፍ ላይ በአካባቢው በተከሰተ ጎርፍ ጣና ሃይቅ ከባህር ወለል በላይ 1887 ሜትር ላይ መድረሱ ተገልጿል።NABU የተሰኘው ተፈጥሮ እንክብካቤ ላይ የሚሠራው የጀርመን ድርጅት ደግሞ በጥናቶቹ እንዳመላከተው የጣና ሀይቅ ከባህር ወለል በላይ ያለው ከፍታ 1840ሜትር መሆኑን ሲጠቅስ በNASA መረጃ ደግሞ ሀይቁ 1830 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ይገኛል። ከሁለቱ መረጃዎች ተነስተን አሁን ደረሰበት የተባለው የሀይቁ ከፍታ በትንሹ  47 በትልቁ ደግሞ የ57 ሜትር ጭማሪ አሳይቷል።በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደተንሸራሸረው የግብጻውያኑ መረጃ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እውነት ቢሆን ባህርዳር ከተማን ጨምሮ በዙሪያ የሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች በውሃ ይዋጡ ነበር።ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ አለመፈጠሩን ግምት ውስጥ ስናስገባ የጣና ሀይቅ 

የውሃ መጠን ጨመረ የተባለበት የከፍታ መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን እንረዳለን።

አሁን ላይ ስራው በይፋ የተፈፀመው  የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሊጠናቀቅ በደረሰበት ወቅት  ላይ ደግሞ  የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች በማለት አደናጋሪ መረጃ ሲሰጡ አድምጠናል።[1]

ግብጽ ለዋሽንግተን ካላት ቅርበትና አጋርነት አኳያ አሜሪካ ግብጽ ጉዳት ያደርስብኛል የምትለውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በገንዘብ ትደግፋለች የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ ዶናልድ ትራምፕ ካይሮ ግድቡን ልታፈርሰው ትችላለች ብለው በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ወቅት መናገራቸውን ስናስታውስ ሀገራቸው በገንዘብ የግድቡን ግንባታ ብትደግፍ ኖሮ እንዲፈርስ ምክረ ሀሳብ ባልሰጡ ነበር እንድንል ያስገድደናል።ከምንም ነገር በላይ ከርቀት የመሰላቸውን ከሚናገሩት ይልቅ የግድቡ ባለቤቶች የሚናገሩትን ማድመጥ ተገቢ ነውና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከፕሬዝደንት ትራምፕ ንግግር በኋላ በሰጠው መግለጫ ግድቡ ያለምንም የውጭ ድጋፍ የተከናወነ መሆኑን አረጋግጧል።[2]

 

ሌላኛው ትኩረት የሚስበውና  ከግድቡ ግንባታ ጅማሬ እስከ ዛሬ ድረስ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሳው ጉዳይ ደግሞ ግብጽ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ልትመታው ትችላለች የሚለው ጉዳይ ነው።በቅርቡ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር' daily news egypt 'ላይ ተናገሩ የተባለው ጉዳይም ይህንን የሚያጠናክር ነው።የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብድላቲ ግብጽ የታሪካዊ የአባይ ወንዝ ድርሻዋን ለማስጠበቅና ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እርምጃ የመውሰድ መብት አላት ማለታቸውን በቅርብ ጊዜ በካይሮ ባለስልጣናት ከተሰጡ ዛቻዎች ለአስረጅነት ጠቀስን እንጂ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ማድረስ የሚለው ሀሳብ ተደጋግሞ የሚሰነዘር ነው።

daily news egypt  ከዚህ ባሻገር ለግብጽ ቅርበት ባለው ' arab center Washington DC' ላይ 'the grand ethiopian renaissance dam and Egypt's militry options' [3]በሚል በካይሮ በእየሩሳሌም የአሜሪካ ዲፕሎማት ሆነው የሰሩት ቻርለስ ዱኔ ባጋሩት ሀሳባቸው ግብጽ የታላቁ የህዳሴ ግድብን የምትመታበት የጦር ሃይል የበላይነት አላት ይላሉ።አሜሪካዊው ዲፕሎማት በጽሁፋቸው የኢትዮጵያን ጦር የቀድሞዋን ሶቬት ህብረትና የዩክሬንን ኋላ ቀር የጦር መሳሪያዎች የታጠቀ ሲሉ አንኳሰውታል።ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰጡትን ንቀት የተሞላበት ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ኢትዮጵያ በጸረ ሽብር ዘመቻዎች በምስራቅ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም ተልዕኮዎች ያሳካቸውን ውጤቶች ግምት ውስጥ አለማስገባታቸው የግለሰቡን ወደ አንድ ወገን ማድላት መረዳት እንችላለን።

የኢትዮጵያን ጦር ዝቅ ያደረጉት አሜሪካዊው ዲፕሎማት የግብጽን የአየርና የምድር ሃይል ግን ያወድሳሉ።ዘመናዊ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቋል የሚሉት ቻርለስ ዱኔ የግብጽ ጦር M1A1 የተሠኘ ታንክ F -16 ተዋጊ ጀት ባለቤት ነውም ይላሉ።በጽሃፊው የተገለጹት እነዚህ የጦር መሳሪያዎች የታላቁ የህዳሴ ግድብን የመምታት አቅም አላቸው ብለን ስንጠይቅ ግን የምናገኘው መልስ አይችሉም ይሆናል። ሀገራት ሙሉ ወታደራዊ ሚስጥራቸው እንደማይገለጽ የሚታመን ነው።ጸሃፊው የዘረዘሯቸውን ግብጽ ታጥቃቸዋለች የተባሉትን መሳሪያዎች ስንገመግም ግን M1A1 የተሠኘው ታንክ ለግንባር ጦርነቶች እንጂ በርቀት የሚገኙ ኢላማዎችን ለመምታት የሚያስችል ሆኖ አናገኘውም። ምክንያቱም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብጽ መካከል ያለው ርቀት 1 ኪሜ በላይ መሆኑና የተጠቀሰው ታንክ ተተኳሹ ይህን ያህል ርቀት መጓዝ አለመቻሉ ነው። [4]

F-16 የተሠኘው ተዋጊ ጀትን በተመለከተ ደግሞ የአሜሪካ አየር ሃይል ባጋራው መረጃ ጀቱ ኢላማን ሊመታ የሚችለው ከተነሳበት ቦታ 860ኪሜ ርቀት ተጉዞ ነው። [5]ይህን መረጃ መሠረት ስናደርግ ግብጽ ለግድቡ ካላት ርቀት አንጻር በተጠቀሰው መሳሪያ ጉዳት የምታደርስበት ዕድል አለመኖሩን እንረዳለን።

የተሳሳቱ መረጃዎቹ ዓላማ  የእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት የስነ ልቦና ጦርነት የበላይነት በመውሰድ ኢትዮጵያውያን በፍርሃት ውስጥ ሆነው የልማት ስራዎቻቸውን እንዳይሰሩ ለማድረግ ያለመ ሆኖ እናገኘዋለን።አሁን ያሉ ተጨባጭ እውነታዎችን ከተመለከትን ግብጽ በውክልና ጦርነት ወይም ውስጣዊ ግጭቶችን በገንዘብ በመደገፍ ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡም በኋላ ሌሎች ፕሮጀክቶችን እንዳታከናውን እንቅፋት ልትፈጥር ትችል ይሆናል እንጂ በቀጥታ በጦር ሃይሏ በኩል የኢትዮጵያን ግቦች የምታደናቅፍበት ሁኔታ ኢምንት ነው።

ከፍ ብለን የታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከሀገር ውጭ የተዛመቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን ዳሰስን እንጂ በሀገር ውስጥም ለፖለቲካዊ አላማ በማህበራዊ ገጾች ተከታይን ለማብዛት የተዛቡ መረጃዎች መቅረባቸውም ሊዘነጋ አይገባም። ሀሰተኛ መረጃዎች ከቅርብም ከሩቅም  ከወዳጅም ከጠላትም ሊፈጠሩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑን በመገንዘብም የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ከፍ ብለው እንዲበሩ የሚያስችሏቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች ላይ የሚዛመቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በተገቢ ሁኔታ መመርመርም በቀጣይ ትኩረት ሊያደርጉበት የሚያሻ ነጥብ ነው።

ጸሐፊ: በላይነህ ዘላለም