የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪወችን ውጤት በተመለከተ የተሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሪፖርት
በ 2017 ዓ.ም በጠቅላላ ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ፈተናውን በሁለት ዙር መውሰዳቸው ይታወቃል። ውጤቱም ይፋ የሚደረግበትን ቀን በተመለከተ ሚኒስትሩ ከወራት በፊት እንዲህ ሲሉ እንደሚከተለው ገልፀው ነበር። "በአማራ ክልል ፈተናውን መውስድ ያልቻሉ ተማሪዎች፣በማረሚያ ቤት ያሉ ታራሚዎች እንዲሁም ዘግይተው ትምህርት የጀመሩ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን በነሐሴ ወር ከወሰዱ በኋላ ጳጉሜ ወር ላይ ውጤት እናሳውቃለን።" ነገር ግን በአንዳንድ ምክንያቶች ውጤቱ በተጠበቁት ቀናት ውስጥ ሳይለቀቅ ቀርቷል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በቲክቶክ፣ በፌስቡክና በቴሌግራም ውጤቱ ይፋ ተደርጓል የሚሉ እና ሌሎች ሀሰተኛ መረጃዎች እየተሰራጩ ስለሆነ ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት ያልቻሉ ተማሪዎች በከባድ ውጥረት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
ሀሰተኛ መረጃዎችና ስርጭታቸው
የ12ኛ ክፍል ውጤትን በተመለከተ ሁልጊዜ በየዓመቱ ወቅታቸውንን ጠብቀው ብዙ ሀሰተኛ መረጃዎች ሲዘዋወሩ ይስተዋላል። በዘንድሮው ዓመት (2017 ዓ.ም ለተፈተኑ) እየተሰራጩ ካሉ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ዋናውና የመጀመሪያው የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ይፋ ተደርጓል የሚል ነው። ከስማንያ ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት "musse Solomon" የተሰኘ የቲክቶክ ገፅ በለቀቀው ቪዲኦ የ2017 ዓ.ም የማትሪክ ውጤት ተለቋል ሲል ገልጿል። ይህ ገፅ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ተከታዮች ያሉትና ዜናን በማቅረብ የታወቀውን Musse Solomon የተባለውን ቲክቶከር ስም በመጠቀም የተከፈተ ሀሰተኛ ገፅ ሲሆን ቪዲኦውም Musse Solomonን በማቀናበር የተሰራ ነው።
ይህን ቪዲኦ ከ ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ በላይ ሰዎች ያዩት ሲሆን አምስት ሺህ ገደማ ሪአክሽን እና ከሁለት ሺህ በላይ ሸር ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ከአራት ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት "ኮሚማ ኮከብ ሚዲያ የተሰኘው የፌስቡክ ገፅ " የ2017 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ዛሬ ጷጉሜ 5/2017 ወይም አርብ መስከረም2 2018 ዓ.ም ጠዋት እንደሚለቀቅ የደረሰኝ መረጃ ያመለክታል።" ሲል ገልጿል።
ሌላኛው ሀሰተኛ መረጃ የ2017 ዓ.ም የ 12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤትን በተመለከተ የተለያዩ አሀዛዊ መረጃዎች ማለትም አማካይ ውጤት፣ጠቅላላ ያለፉ ተማሪዎች ብዛት፣ እንዲሁም ሌሎች ቁጥራዊ መረጃዎችን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል የሚል ነው።እነዚህ ሐሰተኛ አሀዛዊ መረጃዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጩ ሲሆን "insider page"የተሰኘው የቲክቶክ ገጽ በለቀቀው ቪዲኦ "በ2017 የ12ኛ ክፍል ውጤት መግለጫ " በማለት ባለፉት ዓመታት ትምህርት ሚኒስተር የተናገራቸውን የመግለጫ ቪዲኦዎች የዘንድሮ አስመስሎ በመስራት ፓስት አድርጓል።
ይህም ቪዲኦ 19 ሺ ሪአክሽን፣ ከ3 ሺህ በላይ ሼር፣ ሁለት መቶ በላይ ኮመንት እና ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ፌቨራይት አግኝቷል። ከዚህም በተጨማሪ 23 ሽህ ገደማ ተከታዮች ያሉት TOBIAS የተሰኘው የቲክቶክ ገጽ ልክ እንደዚህ አይነት የአሃዛዊ ሀሰተኛ መረጃዎች ቪዲኦ ያጋራ ሲሆን አክሎም ከታች በቀኝ በኩል በተቀመጠው ምስል እንደምንመለከተው የእንቁጣጣሽ ዕለት "የ12ኛ ክፍል ውጤት ሌሊት ስድስት ሰዓት ላይ ይለቀቃል" በማለት የቆዩ የትምህርት ሚኒስተር መግለጫዎችን በማቀናበር ፖስት አድርጓል።

ሌላው ሀሰተኛ መረጃ ውጤት የሚለቀቅበትን ወቅት በመጠበቅና አጋጣሚውም በመጠቀም የሚደረጉ ገንዘብ የማጭበርበር ስራዎች ናቸው። ለምሳሌ ዘጠኝ መቶ ገደማ ተከታዮች ያሉት "ትምህርት ሚኒስትር" የተሰኘው ሀሰተኛ የቴሌግራም ግሩፕ ውጤት ተለቋል የሚል የውሸት መረጃ መልቀቁ ሳያንሳው አድሚሽን ቁጥራችሁን ላኩልኝና በተመጣጣኝ ዋጋ ውጤታችሁን አሳውቃችሗለሁ ሲል መስከረም 2 ቀን የውሸት መልዕክቱን አስተላልፏል።ይህ የማጭበርበር ስራ ውጤት በትክክል ከተለቀቀ በኋላም የሚቀጥል ጉዳይ ነው።
እስካሁን እየተሰራጩ ካሉ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የዘረዘርኳቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ። ነገር ግን ገንዘብ የማጭበርበር ስራ፣ሪሚዲያል በተመለከተ፣ እንዲሁም የዩንቨርስቲ ምደባን በተመለከተው ውጤቱ በትክክል ከተገለፀ በኋላም ሀሰተኛ መረጃዎች እንደሚፈጠሩ ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ባለፉት ዓመታትም በተደጋጋሚ የነበር ክስተት ነው።
እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭታቸው ምን ያህል ነው?
እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭታቸው ከምናስበው በላይ በተለያዩ ማህበሪዋ ሚዲያዎች ማለትም በቲክቶክ፤ ፌስቡክ ቴሌግራም ዩትዩብ እና በሌሎችም ሚዲያዎች ከምናስበው በላይ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ተማሪዎችና ወላጆችም ውጤት ለማወቅ ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ሀሰተኛ መረጃ ሲለቀቅ ከማፍራት ይልቅ ብዙዎች መረጃውን በቀላሉ አምነው ይቀበላሉ። ምንም እንኳን ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆኑ ተማሪዎች መረጃው ሀሰተኛ መሆኑን መለየት ቢችሉም በክፍል ሃገር ወይም በገጠር አካባቢ የሚኖሩት ግን መረጃው ተክክለኛ ነው ብለው ስለሚያምኑ ለእንደዚህ አይነት አሰተኛ መረጃ ተጋላጭ ናቸው።
እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች የሚሰራጩት በዋናነት በማህበራዊ ሚድያ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ በ offline ወይም በወሬ ደረጃ በተለይም ወደገጠሩ ክፍል ሲሰራጩና ሰዎች ሲጨነቁ ማስተዋል ተችሏል፡፡
እንዲህ አይነት መረጃዎች ሀሰተኛ ስለመሆናቸው በምን ማረጋገጥ እንችላለን?
• መረጃውን የሚያስተላልፋበት መንገድ እና የሚጠቀሟቸው የቃላት ስህተቶቾ መረጃው ሀሰተኛ መሆኑን ያመለክታሉ።
• የፈተና ውጤቱን በተመለከተም ትምህርት ሚኒስትር በየትኛውም ኦፊሺያል ገፃቸው ወይም ቴሌቪዥን ላይ ምንም አይነት መግለጫ አለሰጡም።
እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች የሚሰራጩት ለምን ዓላማ ነው?
• ገንዘብ ለማጭበርበር፦ ውጤት በፍጥነት እናይላችኋለን በማለት ገንዘብ እያስላኩ የሚያጭበርበር ስራ የሚሰሩ ብዙዎች አሉ። ለምሳሌ የተማሪውን ውጤት ካዩለት በኋላ በጣም የወረደ ውጤት ከሆነ ብዙ ብር ላክ አለበለዚያ ውጤትህን ሚዲያ ላይ ለቀን እናዋርድሀለን በማለት የሚያስፈራሩና የሚያጭበረብሩ አሉ። እነዛ አጭበርባሪዎችም ብር እንደተላከላቸው የቴሌግራም አካውንታቸውን አጥፍተው ሌላ ማጭበርበሪያ አካውንት ይከፍታሉ።
• የግለሰብን ሚስጥራዊ መረጃዎች ለማግኘት፦ Scam የሆኑ ዌብሳይቶችን ወይም የቴሌግራም ቦቶች እንዲጫኑ በማድረግ የሰዎችን የቴሌግራም አካውንት የሚጠልፋም አሉ።
• ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮችን ለማፍራት፦ ምንም እንኳን ቀጥተኛ የሆነ ገንዘብ ባያገኙም ሀሰተኛ መረጃዎችን በመልቀቅ ብዙ ተከታዮችን ካገኙ በኃላ ያንን ሚዲያ ለሌላ አላማ ማዋል አስበው የሚሰሩም አሉ።
• ባለማወቅ፦ አንዳንድ ግለሰቦች መረጃው ሐሰተኛ መሆኑን ባለማወቃቸው ነገር ግን መረጃው ለወዳጅ ዘመድ ይጠቅማል ብለው በማሰባቸው መረጃውን በሚዲያ እንዲሁም በወሬ ደረጃ ያስተላልፍሉ።
ምን ዓሉታዊ ተፅዕኖዎች አሏቸው?
• ስነልቦናዊ ጭንቀት፦ እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ተማሪዎችን እና የተማሪ ወላጆችን ለብዙ አይነት የስነልቦና ጉዳቶች ይዳርጋሉ። በተለይ የዘንድሮው ውጤት ከበዓል በፊት ስላልተለቀቀ ብዙ ሰዎች ውጥረት ላይ ነበሩ። በቲክቶክ ላይም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ እየተባለ ብዙ meme ተሰርቶባቸው መቀለጃ ሆነው ነበር። ይህም የስሜት መረበሽን ያስከትላል።
• የፋይናንሺያል ጉዳት፦ ብዙዎች ውጤት ከሁሉም በፊት በፍጥነት ለማዎቅ ሲሉ ገንዘባቸውን ለአጭበርባሪዎች ይሰጣሉ።
• አለመታመን፦ እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ትምህርት ሚኒስትር በማህበረሰቡ ዘንድ እንዳይታመን እና የውሸት መረጃዎችን እንደሚያስተላልፍ ተደረጎ ይቆጠራል።
• የሚስጥራዊ መረጃዎች መጋለጥ፦ በአጭበርባሪዎች ምክንያት የአንድ ግለሰብ ብዙ ሚስጥራዊ መረጃዎች ሊዎጡ ይችላሉ። ለምሳሌ የአንድ ሰው የቴሌግራም አካውነት ቢጠለፍ ምናልባት ቴሌግራም ውስጥ የባንክ መረጃዎች ወይም ሌላ ሚሰጥር አስቀምጦ ከነበር በሂደት ሌሎችም መረጃዎች ይሰረቃሉ። ወ.ዘ.ተ..
የመፍትሄ ሃሳብ
እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች የሚሰራጩት ሁልጊዜ በየዓመቱ ስለሆነ ጊዚያዊ ሳይሆን ለወደፊትም የሚሆኑ ዘላቂ መፍትሄዎችን ልንፈልግ ይገባል ለአብነትም
• እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ መረጃዎች ሲያጋጥሙን አምኖ ከመቀበልና ለሌሎች ከማጋራት ይልቅ በመጀመሪያ የመረጃውን ትክክለኛነት ከሚመለከተው አካል ማረጋገጥ ይኖርብናል። ሀሰተኛ ሆኖ ከተገኘም ለራሳችን ብቻ መያዝ ሳይሆን ሀሰተኛነቱን ሌሎች ማሳዎቅ አለብን።
• መረጃ ስንፈልግ ልክ እንደ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያሉ ተዓማኒ ገጾችን መጠቀም፡፡
• ኦፊሻል የሆኑ የመንግስታዊና ትምህርታዊ ምንጮች ገጾቻቸውን መከታተል። ለምሳሌ የትምህርት ሚኒስተር እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሉት ይጠቀሳሉ።
• በየሚዲያው የሚለቀቁ ሊንኮችን አለመክፈት።ትክክለኛ ውጤት የሚታይባቸው አማራጮች ከሚመለከተው አካል ብቻ መቀበል፡፡
ጸሐፊ፡ ኤርሚያስ ውበት