post-thumb

በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ የተሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን

በሠው ልጆች ኑረት ውስጥ ግጭት መፈጠሩ የተለመደ ነው።ፕሮፌሰር ሩዶልፍ ጆሴፍ ሩሜል UNDERSTANDING CONFLICT AND WAR በተሠኘ ጽሁፋቸው የፍላጎት አለመጣጣም ግጭት ከሚፈጠርባቸው ነገሮች አንዱ መንስዔ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያብራራሉ።በግጭቶች ውስጥ የሚሳተፉ ሃይሎች መጨመር ደግሞ ግጭቶች በአጭር እንዳይቋጩ በሠላማዊ መንገድ እንዳይፈቱ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።በግጭቶች ዙሪያ የሚተላለፉ ሀሠተኛ መረጃዎች መበራከት ደግሞ ሌላኛው የግጭት አዙሪቱን የሚያስቀጥልበት ሁኔታን ይፈጥራል።በግጭቶች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሀሠተኛ መረጃ ስርጭት መኖሩን ለመጠቆም council of Europe በግጭቶች ውስጥ ቅድሚያ የሚጎዳው እውነት ነው ማለቱን ልንጠቅስም እንችላለን።

እንደ council of Europe የግጭቱ ተዋንያን አላማቸውን ለማሳካት መሬት ላይ ካለው እውነታ የራቁ ሀሠተኛ መረጃዎችን በተለያየ መንገድ የሚያጋሩበት ዕድል ሰፊ ነው። የመረጃው ታዳሚዎች ደግሞ በሀሰተኛ መረጃዎቹ በመታለል ግጭቶች በሠላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ከማተኮር ይልቅ በፍርሃት ተሸብበው እንዲኖሩም ዕድል ይፈጥራል። ይህ ነገርም በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ተስተውሏል።

በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሠቱ ግጭቶች በሀሠተኛ መረጃ ስርጭት ግጭቶች አድማሳቸው ሲሰፋ የተመለከትን ሲሆን ክቡር የሆነው የሠው ልጅ ህይወትም ሲቀጠፍ ታዝበናል። ምንም እንኳን የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን በህግ ማዕቀፍ ለማረቅ ጥረቶች ቢደረጉም የተፈለገውን ውጤት ግን አስገኝተዋል ማለት አይቻልም።ዛሬም ከግጭቶች ጋር በተያያዘ በሚሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል በእጅጉ ሲጨምር እንደ ሀገር የማህበረ ምጣኔ እንቅስቃሴዎችም (socio economic aspects) ሲጎዱ እየተመለከትን ነው።

ይህን መሠልና  ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች እያስተናገዱ ካሉ የሀገራችን አካባቢዎች ደግሞ የአማራ ክልል ተጠቃሹ ነው። በክልሉ ከሁለት ዓመታት በፊት በመንግስትና በፋኖ ሃይሎች መካከል በተጀመረው ግጭት ከፍተኛ ስብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የደረሠ ሲሆን ዛሬም ግጭቱ መጨረሻው የቱ ጋር እንደሚሆን ባልታወቀ አግባብ ቀጥሏል።በዚህ ውስብስብ የግጭት አዙሪት ዙሪያ በየቀኑ የሚፈጠሩ የሀሰተኛ መረጃዎች ደግሞ ህዝቡ ከእውነት ጋር ቆሞ የመፍትሄው አካል እንዳይሆን ጋርደውታል።

በዚህ ጽሁፍም የክልሉን ህዝብና ከክልሉ ውጭ የሚገኘውን የሀገሪቱን ዜጋ ከዚያም ባሻገር ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የጠራ አቋም እንዳይዝ ያደረጉ ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች በጥቂቱ ይዳሰሳሉ።

በአማራ ክልል ዛሬ ድረስ በቀጠለው ግጭት ከመንግስት ወገን እንዲሁም ከፋኖ ሃይሎች በተደጋጋሚ ግጭቱን የተመለከቱ መግለጫዎች ይሰጣሉ። በመንግስት በኩል የፋኖ ሃይሎችን ቁጥር ቀለል አድርጎ የማየት ሁኔታን ከሚሠጡ መግለጫዎች በተደጋጋሚ ታዝበናል።ምንም እንኳን የፋኖ ሃይሎች ቁጥር በትክክል የሚታወቅ ባለመሆኑ መንግስት የሠጠውን ዝቅተኛ ግምት ለማስተባበል አስቸጋሪ ቢያደርገውም በክልሉ ውስጥ እንደ ልብ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አለመቻሉ ግን ይህ ሃይል መንግስት ከሠጠው ቁመና በላይ ለመሆኑ አመላካች ነው። በፋኖ ሃይሎች በኩል ደግሞ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት የሚሠራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች ሲወጡ አስተውለናል።

በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ከሠማናቸው ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል ባሳለፍነው ዓመት በሰኔ ወር የፋኖ ሃይሎች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን የያዘች ሄሊኮፕተር ጎርጎራ አካባቢ መትቸ በመጣል በርካታ የፌዴራል መንግስት አመራሮችን ገደልኩ የሚለው ጉዳይ ተጨቃሹ ነው።

 

በፋኖ ሃይሎች የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ አሳካሁት ባለው ጥቃት የሀገሪቱን ርዕሰ ብሄር አምሳደር ታየ አጽቀስላሴን ጨምሮ /// ተመስገን ጥሩነህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደን ጨምሮ 27 አመራሮች ህይወታቸው ማለፉም ተሠምቶ ነበር።እዚህ ላይ የዚህ ሃይል የተጠቀሰው ክፍል ቃል አቀባይ የዚህ ክፍል አባል ዮቲዮብ ላይ 132 ተከታዮች ላሉት ኢትዮ ፎከስ ለተሠኘ ቻናል የሠጡትን መግለጫ በአስረጅነት እንጥቀስ።

ይህን ሀሰተኛ መረጃ የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን የተሳሳተ መሆኑን ቢገልጽም ቀድሞ በፋኖ ሃይሎች የወጣው መግለጫ ግን በአስርሽዎች ተከታይ ባላቸው x አካውንት ባለቤቶች በሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾች በብዛት እንዳይጋራ ግን አላስቀረም።

ከሄሊኮፕተር ጥቃቱ ጋር በተያያዘ የተሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ስንመረምር ህይወታቸው አልፏል የተባሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ዛሬ በስራቸው ላይ መገኘታቸው  ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት ህያው የሆኑ ሠዎችን መቅበር ድረስ እንዳለ እንገነዘባለን።ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሏት ሄሊኮፕተሮች ከፍተኛ የመጫን አቅም 26 ሠዎች ሆኖ ሳለ የፋኖ ሃይሎች 27 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል ማለታቸው council of europe እንደሚለው በግጭቶች ውስጥ አውነት ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስባት ማሳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ይህን ጽሁፍ በመጻፍ ሂደት እውነቱን ለማጣራት የዓይን እማኞችን ለማነጋገር ተሞክሯል።

ሀሳባቸውን ከሰጡ መካከል በሄሊኮፕተር አደጋው የተጎዱ ሠዎችን ጎርጎራ ጤና ጣቢያ ያደረሡ ሠዎች የሚገኙበት ሲሆን ሄሊኮፕተሯ ከማረፊያዋ ውጭ መውደቋን ሲያረጋግጡ በፋኖ ሃይሎች እንደተገለጸው በአካባቢው ምንም ዓይነት ፍንዳታ አለመሠማቱ ሄሊኮፕተሯ በመሳሪያ አለመመታቷ አስረጅ ነው።ይህ የፋኖ ሃይሎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትም አለም አቀፍ ተደማጭነት ለማግኘት ያለመ እና የክልሉ ህዝብ በአሁኑ ስዓት በዋናነት የሚጠቀምበትን የአየር ትራንስፖርት በስጋት በመመልከት መንግስት ተዳክሟል በሚል  ተቃውሞ እንዲያሰማ ያለመ አድርገን ልንወስድ እንችላለን።

ሌላኛው በፋኖ ሃይሎች በኩል ተደርጓል በሚል x አካውንት በቡድኑ ደጋፊዎች ሲዘዋወር የነበረው ደቡብ ወሎ ዞን ሀይቅ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ወደመ በሚል የተሠራጨ ሀሠተኛ መረጃ ተጠቃሹ ነው። በእርግጥ በአማራ ክልል በየጊዜው በተለያዩ ቦታዎች በመንግስት በፋኖ ሃይሎች መካከል ግጭቶች ይከሰታሉ። ከግጭቶች መደጋገም የተነሳ ልዩ ክስተቶች ከተከሰተባቸው ቦታዎች ውጭ ግጭቶቹ ብዙ ትኩረት አይስቡም።በሀይቅ ከተማ አቅራቢያ በነበረ ግጭት ተፈጸመ የተባለው ሁነት ልዩ መሆኑም ነው ጉዳዩን ለማጣራት መነሻ የሆነው።

 

  x አካውንት በተሠራጨው ሀሰተኛ መረጃ ሀይቅ ከተማ አቅራቢያ ቆሎ ባቂላ (kollo bakila) በተባለ ስፍራ የሚገኝ የመከላከያ ካምፕ ሙሉ በሙሉ ወደመ  በሚልም ተንቀሳቃሽ ምስልም ተያይዟል።ይሁን እንጂ ሀይቅ ከተማ አቅራቢያ በተባለው ስም የሚጠራ ቦታ አለመኖሩን የጎግል ማፕ መረጃ ያመላክታል።ከዚህ ባሻገርም መረጃውን በማጣራት ሂደት የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የደሴ ቅርንጫፍ ጋዜጠኞችንና የሀይቅ ከተማ ነዋሪዎችን ጠይቀን በሰጡን ምላሽ በተጠቀሰው ስም የሚጠራ ስፍራ በቦታው አለመኖሩን ነው። ከዚህ በመነሳት የሀሠተኛ መረጃ ስርጭቱን ስንመዝነው በምናብ በተፈጠረ ስፍራ ደረሰ በተባለ ጥቃት ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች አለመረጋጋት ውስጥ እንዲገቡ እና የሀገሪቱ ዘብ የሆነውን ሠራዊት ስነ ልቦና ለማላሸቅ መታለሙን መገንዘብ እንችላለን።

ወደ ሌላ ጉዳይ በአማራ ክልል ባለው ግጭትም የተለያዩ ድሎችን የፋኖ ሃይሎች አሳካን ሲሉ በተደጋጋሚ አድምጠናል።ከእነዚህ መካከል የአማራ ክልል ምክር ቤት 6 ዙር 4 ዓመት 10 መደበኛ ጉባዔውን በሐምሌ ወር በባህርዳር ከተማ ሲያካሂድ የፋኖ ሃይሎች ምክርቤቱ ላይ ጥቃት በማድረስ ውጤት አገኘን ማለታቸውን በቅድሚያ እንጥቀስ።

ይሁን እንጂ በተጠቀሰው ጊዜ በምክር ቤቱ ላይ የተሠነዘረ ጥቃት ያልነበረ ሲሆን የምክር ቤቱ ጉባዔም በሠላም መጠናቀቁን ከክልሉ ምክር ቤት አንድ አባል እና በስፍራው ስራ ላይ ከነበረ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የባህርዳር ሪፖርተር ለዚህ ዘገባ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ከዚህ ባሻገርም crisis watch የሐምሌ ወር ሪፖርት[1] ላይ በባህርዳር ከተማ የተመዘገበ ግጭት አለመኖሩ የመረጃውን ሀሰተኝነት ነጋሪ ነው።

በባህርዳር ከተማ የፋኖ ሃይሎች አደረስን ካሉት ጥቃት በጥቃቱ አሳካን ካሉት ግብ ባሻገር በርካታ ሠበር የድል ዜናዎች በብዛት በተለያዩ መገናኛዎች ይሰራጫሉ። በፋኖ ሃይሎች በኩል የተዘበራረቀ እና ወጥ ያልሆነ የመግለጫ ስርዓት መኖሩ ደግሞ ከቡድኑ አመራሮች ወይስ ከደጋፊዎቻቸው መረጃው እንደመነጨ ለማወቅ አዳጋች ያደርገዋል።

የሀሠተኛ መረጃ ስርጭቱ ከብዙ አቅጣጫዎች መሆኑ ደግሞ የእነዚህን መረጃዎች ሀሠተኝነት ለማረጋገጥ ነገሮችን ውስብስብ አድርጎታል።የሆነው ሆኖ እነዚህን መሠል የድል ሰበር ዜናዎች በየትኛውም መንገድ ከማንኛውም ወገን መሠራጨታቸው የክልሉ ነዋሪ በተረጋጋ መንፈስ ኑሮውን እንዳይመራ እና በመንግስት መዋቅር ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠርበት በማድረግ ረገድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱም ይገኛሉ።

ከላይ ከዘረዘርኳቸው ነጥቦች ባሻገር በአማራ ክልል ባለው ግጭት ዙሪያ ከሚዘዋወሩ ተጨባጭ ካልሆኑ ሀሳቦች መካከል የፋኖ ሃይሎች በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ የፖለቲካ ሃይል ሁነዋል የሚለው ነጥብ ተጠቃሽ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች መካከል ማርቲን ፕላውትን መጥቀስ እንችላለን።ጸረ ኢትዮጵያ መንግስት አቋም ያለው ፕላውት 370 በላይ ተከታዮች ባሉት x አካውንቱ ይህን ጉዳይ ለንባብም አብቅቶታል።

በዚህ ጽሁፍ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በተመለከተ የተሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በትቂቱ ለመዳሠሥ ተሞከረ እንጂ ግጭቱ ካለው ውስብስብ ባህሪ እና ከተዋናዮች ብዛት አንጻር የሚሠራጩት መረጃዎች የት የሌለ መሆናቸውን መገንዘብም ያሻል።በክልሉ ያለውን ቀውስ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ እየወሰዱ ያሉ ሀሠተኛ መረጃዎችንም በተገቢ መንገድ መቆጣጠር ስልጣን የተሠጠው አካል ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል።