ጣና ነሽ 2 ወደ ሀገር መግባቷን ተከትሎ የተሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ምን ነበሩ?
መነሻዋ ከቻይና የሆነውና ላለፉት ወራት ከጅቡቲ ተነስታ ባህርዳር የገባችው "ጣናነሽ 2" ጀልባ በማኅበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየ ርዕሰ ጉዳይ ነበር። ይህን የተመለከቱ የተለያዩ ሀሰተኛ ዘገባዎችም ተሰራጭተዋል። በዚህ ሪፖርት የተወሰኑትን እናነሳለን።
ጣናነሽ ላይ ከተወሩ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል ከአንድ ወር በፊት "ደራ ታይምስ" የዩቲዩብ ገጽ ላይ "ጣናነሽ ከተራራው ላይ ወደቀች/ ወደ ኋላ ተንሸራታ ተገለበጠች" ሲል ዘገባ ሰርቶ ነበር።

ከላይ በምስሉ እንደሚታየው ይህ ገጽ የፊት ገጹን (Thumbnail) ምንም ርዕሱን ይህን ቢያደርግም ውስጥ ካለው ይዘት ጋር ግን ርዕሱ ግንኙነት የለውም። ይህም ዝርዝሩን በማየት እይታን ለመፍጠር (Clickbait) የተዘጋጀ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይቻላል።
ሌላው ጣናነሽን በተመለከተ ሲሰራጭ የነበረው ሀሰተኛ መረጃ በፌስቡክ ብዙዎች የተቀባበሉት ጣናነሽ ወደ ጣና ሀይቅ ገብታ ስራ ጀመረች የሚለው መረጃ ነው።

ከላይ በምስሉ እንደምትመለከቱት ምስሉ በጣም አሳሳች በሆነ መልኩ የቀረበ ነው። ትልልቅ ተከታይ ያላቸው የሚዲያ ሰዎች ሳይቀር ይህንን ፎቶ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት በስፋት አሰራጭተውታል።

ከላይ ካሉት በስተቀኝ ያለው ምስል ጣና ነሽ ሁለት ወደ የብስ ስትመጣ የተነሳውን ትክክለኛ ምስል በመጠቀም የተዘገበ ሲሆን በአንጻሩ ከጎኑ ያለው ምስል ደግሞ ተመሳሳይ ምስል ሆኖ ጣና ላይ ስለማረፏ ይገልጻል። ይህም በ ውሸት ግንኙነት (False Connection) የተሰራጨ መረጃ ነው።

ከላይ ያሉት ሁለት ምስሎች የሚያሳዩት ደግሞ የመጀመሪያው ጣና ነሽ አሁን ላይ በጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኝበትን ትክክለኛ ምስል ሲሆን በጎን ያለው ይሄንኑ ምስል በ AI ወደ ቪዲዮ በመለወጥ ወደ ሐይቁ ስትገባ የሚያሳይ ነው።
ይህን በተመለከተም የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 30 ቀን 2017 መግለጫ የሰጠበት ሲሆን ጣና ነሽ 2 ገና ወደ ሐይቁ አለመግባቷንና የሚሰራጨው ፎቶ ውሸት እንደሆነ ገልጾ ነበር።
የዚህ ሀሠተኛ መረጃ አላማ የተመልካች ቀልብ ለመሳብና የተሻለ እይታ ለማግኘት ተብሎ የተሰራጨ ነው ማለት ይቻላል።