post-thumb

በሰው ሰራሽ አስተውህሎት የተሰሩ የዳይላን ፔጅ የህዳሴ ግድብ ንግግሮች

በቅርቡ በቲክቶክ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምረቃ የሚገልጹ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስፋት ተሰራጭተው ነበር። ቪዲዮዎቹ፣ የዓለም አቀፍ ዝና ባለው አሜሪካዊው ቲክቶከር “Dylan Page” ስለ ግድቡ ሁኔታ እየተናገረ ነው የሚል ሃሰተኛ ይዘት ነበራቸው።

ብዙዎች እነዚህን ቪዲዮዎች እውነት መስሏቸው በስሜት አስተያየት ሲሰጡ እና ሲያጋሩ ታይተዋል። ከእነዚህም መካከል፣ የቪዲዮዎቹን ሃሰተኛነት መለየት የቻሉ ቢኖሩም፣ በቀላሉ አምነው የተቀበሉ እና የተደናገጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም።

ከሃሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጋር ተያይዞ ያለው እውነታ ምንድን ነው?

 “Brooknews” የተሰኘው ኢትዮጵያዊ ቲክቶከር  ግድቡ የዓለም አቀፍ ሚድያ ትኩረት እንዲያገኝ በሚል መልካም ዓላማ ኢትዮጵያውያን የ' Dylan page' ቪዲዮዎች ላይ በመግባት በሃሳብ መስጫ ስለ ግድቡ ቪዲዮ እንዲሰራላቸው እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርቦ ነበር።(https://vm.tiktok.com/ZMADEfQa8/)

ይህንን ሀሳብ ተከትለው ሌሎች ተጠቃሚዎች የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም' Dylan page' ገና ቪዲዮ ሳይሰራ እነሱ ልክ እንደሰራ አስመስለው የሃሰት ቪዲዮዎችን አሰራጭተዋል። ከቪዲዮዎቹ መካከል

 https://vm.tiktok.com/ZMADKnA7C/

https://vm.tiktok.com/ZMADK3kTm/

የተለያዩ የፎረንሲክ ትንተናዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሰው ሰራሽ አስተውህሎት (AI) በመጠቀም የተሰሩ ናቸው። በቪዲዮው ላይ የሚሰማው የ'Dylan page' ድምጽ ከከንፈሩ እንቅስቃሴ ጋር ፈጽሞ አይገጣጠምም። ይህም ቪዲዮው ከእውነት የራቀ ቅንብር (Edit ) መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

የተሳሳተው መረጃ ምን ያስተምረናል?

በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በተደረገ ምላሽ መሰብሰብ  የሃሰተኛ መረጃው ምን ያህል ተጽዕኖ እንደፈጠረ መረዳት ይቻላል።  አንዳንድ ሰዎች የቪዲዮውን ሃሰተኛነት ለመለየት ያልተለመደ የድምጽ እና የከንፈር እንቅስቃሴን እንደ ፍንጭ ተጠቅመዋል። ይህ ደግሞ በዲጂታል ሚዲያ ክህሎት ላይ ኢንቨስት ማድረጋችን ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያሳያል።

ሌሎች ደግሞ የቪዲዮዎቹን እውነትነት በቀላሉ አምነው ነበር። ይህ የሚያሳየው የሃሰተኛ መረጃ ፈጣሪዎች የሰዎችን ትኩረት እና ስሜት በቀላሉ የመጠቀም አቅማቸውን ነው።

መሰል የሃሰት ቪዲዮዎች ሲገጥሙን ምን እናድርግ?

የቪዲዮው ይዘት ከአፉ እንቅስቃሴ ጋር ካልተጣጣመ ወይም ድምፁ ሰው ሰራሽ ከሆነ መጠራጠር ያስፈልጋል።በተጨማሪ የተለቀቀበት አካውንት የተረጋገጠ (verified) ነው ወይ? ሌሎች ብዙ ተዓማኒነት ያላቸው ቪዲዮዎችን አቅርቧል ወይ? ብለን መጠየቅ ይገባል።ሃሰተኛ መረጃዎች በፍጥነት ስለሚሰራጩ  አጠራጣሪ ሆኖ ሲገኝ ሳይረጋገጥ ለሌላ ሰው ከማጋራት መቆጠብ ይገባል።

ፀሃፊ: ሃይሉ