በኢትዮጵያ ይገነባል የተባለውን የኒውኪሊየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተከትሎ የተሰራጩ አሳሳች መረጃዎች
ኢትዮጵያ በቅርቡ የታላቁን የህዳሴ ግድብ አጠናቃ ለአገልግሎት ማብቃቷ የሚታወስ ነው። ታዲያ በዚሁ የህዳሴው ግድብ የምርቃት ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) እንደ ሀገር በቀጣይ ይሰራሉ ተብለው የታቀዱ ፕሮጀክቶችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን ከነዚህም በቀጣዮቹ አመታት ተግባራዊ ይደረጋሉ ከተባሉ ፕሮጀክቶች መካከል ለኃይል አቅርቦት የሚውል የኒውኪሊየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተጠቃሽ ነው።
ይሁን እንጂ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሃሰተኛና አደናጋሪ መረጃዎች ፌዝና ቀልድን ጨምሮ በተለያየ መልኩ በየማህበራዊ ሚዲያው ሲዘዋወሩ ለመታዘብ ችለናል።
ኢትዮጵያም እንደ ኢራን?

ይህ ከላይ በምስሉ የምትመለከቱት '' የኛ ሰው ሚዲያ'' የሚል ከ238ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ በመስከረም 1 2018 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ያጋራው መረጃ ነው። '' ኢትዮጵያ ኒውክለር ልታበለፅግ ነው ኢራን ሆይ መጣንልሽ'' የሚል ይዘት ያለው ይህ መረጃ ባለማወቅም ይሁን አውቆ ለሌላ አላማ ለመጠቀም የተሰራጨ ሃሰተኛ መረጃ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚንስትሯ በኩል የፕሮጀክቱን ውጥን ስትገልፅ የኒውኪሊየር ኃይል ማበልፀጊያ የምትሰራው ለሰላማዊና የአለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ኤጀንሲ በሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች ላይ ተመርኩዛ ለኃይል ፍጆታ ብቻ የምትጠቀምበት እንጂ ''የኛ ሰው ሚዲያ'' እንዳሰራጨው አይነት ለጦር አላማ የሚውል የኒውኪሊየር መሳሪያ ለመታጠቅ እንዳልሆነ በግልፅ ተቀምጧል።
ኢትዮጽያ የኒውኪሊየር ኃይል ማበልፀግ ጀምራለች?
' Ethio jeberti media' የሚል ከ9ሺ በላይ ሰብስክራይበር ያለው የዩቲዩብ ቻናል መስከረም 1 ቀን 2018 ኢትዮጵያ ኒውኪሊየር ማበልፀግ መጀመሯን የሚገልፅ መረጃ አጋርቷል። በዚህ የዩቲዩብ ቻናል የቀረበው መረጃ ኢትዮጵያ ኒውኪሊየር ማበልፀግ መጀመሯን ከግድቡ ምርቃት ጋር አያይዞ ያቀረበ ሲሆን ይህም መረጃ ወቅቱን ያልጠበቀና ሆን ተብሎ ለግል ጥቅም ሲባል (እይታን ለማሳደግ ) በፊት ገፅ ወይም በአርእስትነት በማስቀመጥ የተጋራ ሃሰተኛ መረጃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በእለቱ ባቀረቡት ንግግር ላይ ይህ ፕሮጀክት በቀጣዮቹ አመታት ሊተገበር በእቅድ መያዙን እንጂ ኢትዮጵያ የኒውኪሊየር ኃይል ማበልፀግ መጀመሯን አይገልጽም።
አንዳንዶች ባለማወቅ የተሳሳተ ሃሳብ ሲሰጡ ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የሚጠቀሰው የኒውኪሊየር ኃይል ከጦር መሳሪያነት ባለፈ ለኃይል አቅርቦት ምንጭነት በሰላማዊና ህጉን በተከተለ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል አለማወቅ ወይንም የግንዛቤ እጥረቶች መኖር ነው።
ስለሆነም የመረጃዎቹ ባለቤቶች መረጃውን ከማጋራታቸው በፊት ስለመረጃው በቂ ግንዛቤ ቢኖራቸውና እንዲሁም መረጃ ፈላጊው ህብረተሰብም ስለሚከተሏቸው የማህበራዊ ትስስር ገፆችና ስለ መረጃዎቻቸው አይነትና ይዘት የማጣራትና የመመርመር ዝንባሌን ቢያዳብሩ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መዋጋትና መቀነስ ብሎም በሂደት መግታት ይቻላል።
ፀሃፊ: አዩብ ካዛሊ