በመስከረም ወር በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር መንገዶች የተሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች
በመስከረም ወር በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት ከተሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክን በተመለከተ ሲዘዋወር የነበረው መረጃ ተጠቃሹ ነው።ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የጤና ችግር ስለገጠማቸው ሌላ ሰው እንዲሾም ጥያቄ አቀረቡ በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር መንገዶች በስፋት ሲዘዋወር የነበረን መረጃ በመስከረም ወር በስፋት ታዝበናል። ከቅዱስነታቸው የመልቀቅ ካለዚያም አቃቢ መንበር እንዲሾም ከመጠየቃቸው ጋር በተያያዘም ከጀርባ ሌላ ፖለቲካዊ ግፊት እንዳለ የይሆናል መላ ምቶችም አብረው ተዘዋውረዋል።ይህን ጉዳይ ለታዳሚዎች ካደረሡ አካላት መካከል በyoutube ከ150ሽ በላይ ተከታይ ያለው EOT React የተሰኘ ቻናል ተጠቃሹ ነው።
https://youtu.be/YsU6QaRGrTk?si=Vfnbw-UfLclPgcmP
በዚህ የዩቲዩብ ቻናል ቅዱስነታቸው አቃቢ መንበር ይመደብልኝ ብለዋል የሚል ና ሃላፊነቴን ማከናወን አልችልም ና ሌላ ሰው ይተካ ብለዋል በሚል ሁለት ዓይነት ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ ፣ በቻናሉ ላይም ይህን ሀሳብ የሚያጠናክሩ የሌሎች ሰዎች የግል ምልከታን የያዙ ቪዲዮዎችም በዋቢነት ተያይዘዋል። በዚህ ቻናል ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ አቡነ ሳውሪዎስ የተባሉ ጳጳስ ሊሆኑ እንደሚችሉም የይሆናል መላምት ተሰንዝሯል።ይህን መላምት እንያዘውና የቅዱስነታቸውን ጉዳይ በተመለከተ ሌላ መረጃ ያጋራን የ youtube ቻናል እንመልከት።
ክብረ ተዋህዶ ሚዲያ የተሠኘ ከ30ሽ በላይ ተከታዮች ያሉት ቻናልም "ሠበር አቡነ ማቲያስ ፕትርክና በቃኝ አሉ" በሚል ለታዳሚዎቹ መረጃን በማድረስም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ልንጠቅሰው የምንችለው ቻናል ነው።
https://youtu.be/oECDJaF6RdQ?si=QqTNYVwA9O4SpXIS
በዚህ መረጃ የአንድ ግለሠብ የግል ምልከታም ተካቶ ያስተዋልን ሲሆን በመረጃው ቅዱስነታቸው አቡነ ሳሙኤል የተባሉ ጳጳስን ለአቃቢ መንበርነት ማጨታቸውም ተጠቅሷል።አቡነ ሳሙኤል የተባሉት ጳጳስ ትውልዳቸው ትግራይ ክልል ነው የሚለው መረጃው ይህን መሳይ የስልጣን ሽግግር በብሉይ እንጂ በአዲስ ኪዳን ሊኖር አይገባም ሲልም ይተቻል።
ምንም እንኳ youtubeን ጨምሮ በፌስቡክ ና በሌሎች የማህበራዊ ትስስር መንገዶች ቅዱስነታቸው ኃላፊነት በቃኝ አሉ ና አቃቢ መንበር ይመደብልኝ ሲሉ ጠየቁ በሚል በስፋት መረጃው ቢዘዋወርም የፓትርያኩ ልዩ ጽህፈት ቤት ግን ባወጣው መግለጫ ቅዱስነታቸውን በተመለከተ እየተዘዋወረ የሚገኘው መረጃ ፈጽሞ ስህተት ነው ሲል አጣጥሎታል።የፓትርያኩ ልዩ ጽህፈት ቤት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሠጠው መግለጫም በተለያዩ መንገዶች ለህዝብ እንዲደርስ ተደርጓል።
https://www.facebook.com/100064860301477/posts/1258463752992290/?app=fbl
https://www.facebook.com/100069412705425/posts/1120407703616309/?app=fbl
https://www.facebook.com/100064812606340/posts/1264255882411487/?app=fbl
ምንም እንኳን ከላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ስልጣን በቃኝ አሉ ና አቃቢ መንበር እንዲሾምላቸው በደብዳቤ ጠየቁ በሚል የተሠራጩት መረጃዎች ሀሰት መሆናቸውን ቤተ ክርስቲያኗ ብታሳውቅም በጉዳዩ ዙሪያ ስማቸው የተጠቀሱት የአቡነ ሳውሪዎስ ና የአቡነ ሳሙኤል ጉዳይ ግን ትኩረት የሚስብ ሆኖ እናገኘዋለን።
ሁለቱ ጳጳሳት ለቅዱስነታቸው ቦታ መታጨታቸው ሰሙን ስንመለከተው ችግር የለውም ብለን እንድናልፍ ቢያደርገንም ወርቁን ስናጤን ግን በሀገራችን ያለውን የብሄር ፖለቲካ የበለጠ ለማጦዝ የታለመ ነው። በመረጃዎቹ አቡነ ሳውሪዎስ ብሄራቸው ኦሮሞ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በሂደቱ መንግስት እጁ አለበት የሚለውን ለመጠቆም እንደታለመ መረዳት ይቻላል።ይህ በራሱ መንግስት በሃይማኖት ተቋማት ጣልቃ አይገባም የሚለውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ እየጣሠ ነው የሚለውን በቤተክርስቲያኗ ምዕምናን ውስጥ በማስረጽ ለመንግስት የሚኖርን ቅቡልነት ለመቀነስ ዕድልን የሚፈጥርም ነው።በሌላኛው ጫፍ ስማቸው የተጠቀሰው አቡነ ሳሙኤል ብሄራቸው ትግሬ ነው የተባለ ሲሆን የቤተክርስቲያኗ ስልጣን በዘር እየተላለፈ ነው የሚለውን በመጠቆም በምዕምኗ መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር መረጃው እንደተሠናዳ ያሳያል።ይህ ቅዱስነታቸውን የተመለከተው መረጃ የቤተክርስቲያኗን ምዕምናን ማህበራዊ እረፍት ነስቷቸው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ፌስቡክን በመሠሉ የማህበራዊ ትስስር መንገዶች ስሜታቸውን ሲገልጹም አስተውለናል።


በመስከረም ወር የታዘብነው ሌላኛው ሀሰተኛ መረጃ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ጉዳይ ነው።በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት ና ነፍጥ ባነገቡ ሃይሎች መካከል ግጭቶች መኖራቸው ለማንም የተሠወረ ሀቅ አይደለም።ታዲያ ግጭቶችን መነሻ በማድረግም በየቀኑ በርካታ መረጃዎች ይሠራጫሉ።ከእነዚህ መረጃዎች መካከል በyoutube ከ 40ሽ በላይ ተከታዮች ያሉት Ethio post የተሠኘ ቻናል "ፋኖ በኦሮሚያ የጦር ቤዝ መሠረተ ፤አቶ ሽመልስ የፈሩት ደረሰ " በሚል ለታዳሚዎች ያደረሰውን መረጃ ልንጠቅስ እንችላለን።
https://youtu.be/HNPGRcSGogM?si=xASs3jr7bGNIh9_M
በዚህ ቻናል መረጃ ፋኖ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን 3 ወረዳዎችን ተቆጣጠረ በሚል የተገለጸ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ደግሞ አምስት ወረዳዎችን መቆጣጠሩን በዘገባው አመላክተዋል።በዚህ ዘገባ ሁለቱ ሃይሎች ተቆጣጠሯቸው የተባሉት ወረዳዎች በስም አለመጠቀሳቸው የዘገባውን ተዓማኒነት የሚቀንስና በዘገባው ላይ ጥርጣሬን የሚያስነሳ ነው።በዘገባው የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ስለ ሁኔታው ለቪኦኤ(VOA) ና ለዶቼቬሌ(DW) ተናገሩ ተብሎ የድምጻቸው ቅጂ ሳይያያዝ በዋቢነትም ተጠቅሰዋል።ይሁን እንጂ የዞኑ አሰተዳዳሪ በተባለው ጊዜ ወይም ዘገባው በተሠራበት ወቅት ለሁለቱ የዜና ተቋማት የሠጡት ቃለ ምልልስ አለመኖሩን ከዜና ተቋማቱ ክምችት (archive) ማረጋገጥ ተችሏል።


ከእነዚህ ሁኔታዎች በመነሳት ዘገባው ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የተሠራ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ወዲህ በታጣቂ ሃይሎቹ ተያዙ የተባሉት ቦታዎች በዘገባዎቹ አለመመላከቱ ወዲያ የተጠቀሱት የመንግስት የስራ ሃላፊ ንግግራቸው በአስረጅነት ሳይያያዝ የተሠራው የዚህ ቻናል ዘገባ ማዕከላዊ መንግስት ተዳክሟል የሚል ሀሳብን ለማሳየት እና በተገፍቻለሁ ስሜት በሁለቱ ብሄሮች ማለትም በአማራ ና በኦሮሞ ብሄሮች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ ያለመ ሀሠተኛ መረጃ እንደሆነም መገንዘብ እንችላለን።ይህ ዘገባ በዩቲዩብ ቻናል ለታዳሚዎች የደረሠ ሲሆን መረጃውን ባለማጋራት ስርጭቱን መግታት የተመልካቾቹ ሃላፊነት ሲሆን ዘገባው ሀሰተኛ መሆኑን ሪፖርት ማድረግም ይገባቸዋል።
ወደ ሌላ ሀሠተኛ መረጃ ስንሻገር ደግሞ አራዳ ታይምስ(Arada times) የተሠኘ የፌስቡክ ገጽ በመስከረም ወር ያጋራውን መረጃ እናገኛለን።ይህ ገጽ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑትን ማሳድ ቡሎስ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ ከ38 ሽ በላይ ወዳጆች ና ከ44 ሽህ በላይ ለሚሆኑ ተከታዮቹ ያጋራው መረጃ ስሜታዊነት የሚታይበትም ነው።ገጹ ባጋራው ጽሁፍ "ኢትዮጵያ ከ አሜሪካ ጋር በመወያየቷ ባንዳ ና ኤርትራን አስደነገጠ" የሚል ርዕስም ሠጥቶት ተመልክተናል።በእርግጥ በተጋራው ጽሁፍ የባለስልጣኑ ስም ባይጠቀስም ከግርጌ የተያያዘው ምስል ግን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ና የማሳድ ቡሎስ መሆኑ ጉዳዩ ከሁለቱ ውይይት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አስረጅ ነው።
https://www.facebook.com/100075868586807/posts/801392312399714/?app=fbl
የተጠቀሱት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ቆይታቸው በኋላ ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።ይህን ጉዳይ ኤርትራም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምባሳደሯ የ x አካውንት በኩል ገልጻለች።

ማሳድ ቡሎስ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት ምን መልክ እንደነበረውም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በኩልም እንዲህ ገልጸውታል።
https://www.facebook.com/us.emb.addisababa/videos/2197759587302909/?mibextid=rS40aB7S9Ucbxw6v
ማሳድ ቡሎስ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ተባብረው በሚሠሩበት ሁኔታ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለመ እንደነበረም በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ተገልጿል።አራዳ ታይምስ (arada times) በተሠኘው የፌስቡክ ገጽ ግን የሁለቱ አካላት ውይይት ፋኖን ና ኤርትራን አስደነገጠ መባሉ የተሳሳተና በአመክንዩ ያልተደገፈ መሆኑን ተመልክተናል።ይህ ገጽ ለጽሁፉ የሠጠው ርዕስም emotional headline ሲሆን የተጠቀሱት ሃይሎች በምን ምክንያት ድንጋጤ እንደገባቸውም በዝርዝር አልተቀመጠም።ይህ የዚህ ገጽ አሳሳች ና የፈጠራ መረጃም ፖለቲካዊ ውግንና የሚታይበት እና በተጻራሪ የቆሙ ሃይሎችን ለማዋረድ የተሠራጨ እንደሆነ አምናለሁ።ከዚህ ባሻገርም ፋኖ የተባለው ሃይልና የኤርትራ መንግስት በአንድ ላይ መቆማቸውን ለማመላከት የታለመ እንደሆነም ይሰማኛል።ይህን መሳይ የሀሠተኛ መረጃም በግጭት ጫፍ ላይ ቁመዋል የሚባሉትን ሁለት ሀገራት ህዝቦች ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያበላሽ ና ከድጡ ወደ ማጡ የሚመራም ነው።እኒህን መሠል መረጃዎችም እንደወረደ ከመቀበልም ጉዳዩን አጽንኦት ሠጥቶ መመርመር የገጹ ተከታዮች ይጠበቅባቸዋል።ይህን ተግባር መፈጸም ና ሀሠተኛ ጽሁፎቹን አለማጋራትም ገጹ ኃላፊነት የተሞላባቸው ና ተዓማኒ መረጃ እንዲያጋራ የማድረግ ዕድል ይኖረዋል።
በመስከረም ወር ከተመለከትናቸው ሀሠተኛ መረጃዎች መካከል የተሳሳቱ የስራ ማስታወቂያዎች ትኩረት የሚስቡ ነበሩ።የቀጣሪ ድርጅቶች ስም ባልተገለጸበት የበዙ የስራ ማስታወቂያዎች ከፍተኛ የደመወዝ መጠን ያላቸው አማላይ የስራ ማስታወቂያዎችም የተመለከትንበት ሁኔታ አለ።እንደ አብነት ያክል ከ 9 ሽህ በላይ ወዳጆችና 10 ሽህ የሚጠጉ ተከታዮች ባሉት ስራ አፈላላጊ በተሠኘ የፌስቡክ ገጽ የተጋራን የስራ ማስታወቂያም ልናነሳ እንችላለን።
https://www.facebook.com/100067673065017/posts/1130018219263936/?app=fbl
በዚህ ገጽ በተጋራው መረጃ ላይ ከግርጌ የተያያዙት ምስሎች ህጋዊ የስራ ማስታወቂያዎች ሲሆኑ ከላይ ስለስራዎቹ የተዘረዘረው ጽሁፍ የማይመሳሰል መሆኑ በተሳሳተ ትስስር(false connection) ሠዎችን ለማሳሳት መታለሙን እንረዳለን።በዚህ የስራ ማስታወቂያ ላይ አግኙን ተብለው የተቀመጡ የስልክ አድራሻዎች ሲኖሩ ስለ ጉዳዩ በመደወል በተደረገው ማጣራት ለምዝገባ ክፍያ የሚፈጸም ሲሆን ተግባሩን የሚፈጽሙት አካላትም አዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።ምዝገባው የሚከናወነው ደግሞ በአካል በመገኘት መሆኑም ተረጋግጧል።
ይህ ሀሰተኛ መረጃ በተለይ ክፍለሀገር ለሚኖሩ ስራ ፈላጊዎች አካባቢያቸውን ለስራ ፍለጋ እንዲለቁ በማድረግ ለችግር የሚያጋልጥበት ዕድልም አለው።በመሆኑም በመሠል ማስታወቂያዎች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከመጋለጥ ራስን ለማዳን ማስታወቂያዎቹን በተገቢ መንገድ መመርመር አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል።
ፀሃፊ: በላይነህ ዘለአለም