post-thumb

የቤት ለቤት አስጠኚ አገናኝ አጭበርባሪ ደላሎች ጉዳይና ከፓስፖርት ማውጣት ጋር በተያያዘ የቀጠሉ የማጭበርበር ስልቶች

በመስከረም ወር 2018 ከተሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች መካከል የቀጠለው የፓስፖርት ማውጣት የማጭበርበሪያ ስልት፣ የቤት ለቤት አስጠኚ አገናኝ ነን የሚሉ ደላሎችን እንደዚሁም የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን የተመለከቱ ጉዳዮች ይገኙበታል።

 የቤት ለቤት አስጠኚ አገናኝ ነን የሚሉ አጭበርባሪ ደላላዎች

ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ ሲሉ ለልጆቻቸው የቤት ለቤት አስጠኚ (home tutor) መቅጠር ጀምረዋል። እነዚህም የቤት ለቤት አስጠኚዎች አብዛኞቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሲሆኑ ከነዚህም በተጨማሪ ተመርቀው ስራ ያጡ ወጣቶች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ መምህራን፣ እና ሌሎችም የመንግስት ሰራተኞች ይካተታሉ። ሆኖም ወላጆች እነዚህን አስጠኚዎች የሚያገኟቸው በቀጥታ ሳይሆን በደላላዎች በኩል ነው። ደላላዎችም አስጠኚዎች ስራውን ከመጀመራቸው በፊት የኮሚሽን ቅድመ ክፍያ በባንክ እንዲያስተላልፉላቸው ያደርጋሉ። ነገር ግን ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም ሰዎችን የሚያጭበረብሩ ደላላዎች በርካታ ናቸው። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች ላይ እየተደረገ ያለ የማጭበርበር ሁኔታ እንደሚከተለው እንመልከት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከ2016 .ም ጀምሮ በግልም ሆነ በድርጅት መልኩ ቤት ለቤት አስጠኚ (home tutor) አገናኝ ነን እያሉ በየቦታው እና በቴሌግራም (መረጃ የምናገኝበት የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ግሩፕ ላይ ሳይቀር) ማስታወቂያዎች ሲለቀቁ እንመለከታለን። ብዙ ተማሪዎችም ቅድመ ክፍያ እየከፈሉ የስራ ዕድል እያገኙ ነውበተቃራኒው ደግሞ በዩኒቨርስቲው በሁሉም ካምፓሶች የሚማሩ ብዙ ተማሪዎች ገንዘባቸውን የተጭበረበሩ ይገኛሉ  ብዙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምስኪን ወላጆቻቸውን ገንዘብ ላለማስቸገር ሲሉ  ገንዘብ ለማግኘት ስለሚጥሩ  ስራውን ለመጀመር ከዘመድ ወይም ከጓደኛ ገንዘብ ተበድረው ቅድመ ክፍያ ይከፍላሉ። ነገር ግን ቅድመ ክፍያው በባንክ ከገባላቸው  በኋላ ደላላዎች ቴሌግራም አካውንታቸውን ያጠፋሉ፤  ሉንም ሆነ ግሩፑን አጥፍተው ይሰወራሉ  ጥሩ የስራ እድል አገኘን ብለው እስከ 4,000 ብር ቅድመ ክፍያ ከፍለው የተሸወዱ ተማሪዎች በርካቶች ናቸው እነዚህ አጭበርባሪ ደላላዎች በባዶ ምንም የስራ ሁኔታ ሳይኖር ለሁሉም ካምፓሶች ቅርብ በሆኑ የተለያዩ ቦታዎች ስራ እንዳለ በማስመሰል በተማሪዎች ቴሌግራም ግሩፖች እንዲሁም በራሳቸው ሚዲያዎች ላይ የውሸት ማስታወቂያዎችን ፖስት ያደርጋሉ። ከዚያ በኋላ በአንድ የስራ ገበታ እንኳን ብዙ አመልካቾች ሲጠይቋቸው ሁሉንም በመቀበል ከሁሉም አመልካቾች ቅድመ ክፍያ አስልከው ይጠፋሉ። ይህም ክስተት ያጋማቸው በርካታ ተማሪዎች ለቤተሰብ ለመናገር  እየተሳቀቁ ችግራቸውን በውስጣቸው አፍነው ይዘው ቀርተዋል። በዚህም ዙሪያ እነዚያን ሀሰተኛ እና አጭበርባሪ ገፆች ለመለየት ይረዳን ዘንድ ብዙ የተጭበረበሩ ተማሪዎች ገፆችን እንዲጠቁሙን የጠየቅን ሲሆን ለምሳሌ ያህል የቢዝነስና ኮሜርስ ካምፓስ የተማሪዎች ፕሬዘዳንት ሀሳቡን እንዲህ ሲል ገልጿል። "በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ የተጭበረበሩ የማውቃቸው ተማሪዎች አሉ እኔም ራሴ ተጭበርብሪያለሁ። Family tutor የሚባል የቴሌግራም ገፅ ባወጣው ማስታወቂያ አመልክቼ ነበር። ነገር ግን ብር ካስተላለፍኩ በኋላ አስጠኚ የሚፈልጉትን ወላጆች ሳያገናኙኝ ስልካቸውን ዘግተው ጠፍተዋል።" ብሏል።

 ከዚህም በተጨማሪ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ የጤና ተማሪ እንዲህ ብሏል ። " እኔ የተጭበረበርኩት ከወራት በፊት ሲሆን የተሌግራም ገፁ scholars home tutor ይባላል። ያንጊዜ በሰዓቱ እንደሚሸውዱኝ እየጠረጠርኩ ነበር ነገር ግን ስራ ለመስራት ካለኝ ፍላጎት የተነሳ እና ደላላውም በላከልኝ ማሳመኛ ቃላቶች ምክንያት ቅድመ ክፍያውን እያቅማማሁ ከፈልኩ። ልክ ብር እንዳስገባሁ ወዲያውኑ የደላላው አካውንትም ቻናሉም ጠፍቷል።"ብሏል

ይህ ተማሪ የተጭበረበረበትን ማስታወቂያ እንደሚከተለው በምስል አጋርቶናል።ነገር ግን አሁን ላይ ቻናሉ ጠፍቷል።

የእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እና ተፅዕኖእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች የሚሰራጩት በስፋት በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም በሌሎች ትልልቅ ከተሞችም መሰራጨት እየጀመሩ ነው። "በአዲስ አመት አዲስ የስኬት ጉዞ ጀምሩ" የሚል የማታለያ ቃል በመጠቀም ከሌላው ወቅት አንፃር መስከረም ወር ላይ በሰፊው ይሰራጫሉ። የሚሰራጩበት መንገድ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማለትም በቴሌግራም፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ ሲሆን በስፋት የሚሰራጩት ግን በቴሌግራም አማካኝነት ነው። በተጨማሪም በየቦታው ወረቀት በመለጠፍ በስፋት ማስታወቂያዎች ይሰራሉ። በ offline የሚሰራጩበትን መንገድ ስንመለከት አስጠኝ እናገናኛለን የሚሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የወረቀት ማስታወቂያዎች በሁሉም ክፍለ ከተማዎች፣ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ፖሎች፣ በትምህርት ቤት በሮች እንዲሁም በመኖሪያ ኮንዶሚንየም አካባቢዎች ተለጥፈው  ይስተዋላሉ። ነገር ግን እነዚህ ማስታወቂያዎች ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ ነው። እነዚያን የoffline ማስታወቂያዎች በማየት የሚሸወዱት በብዛት ተመርቀው ስራ ያላገኙ ወጣቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ሲሆኑ በኦንላይን ማለትም በቴሌግራም የሚለቀቁት ደግሞ የግቢ ተማሪዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። ይህንን ዘዴ የተጠቀሙበት ምክንያት ውጭ ላይ የሚለጠፉ  ማስታወቂያወችን የግቢ ተማሪዎች የማየት ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን በመገንዘብ ነው። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ1400 በላይ ተከታዮች ያሉት "SEFERE SELAM Student Council" የተሰኘው የጤና ተማሪዎች የጋራ ግሩፕ ላይ ሁሉም ተከታዮች ወደ ግሩፑ መልዕከት forward ማድረግ ስለሚችሉ በየሳምንቱ ከአስር ያላነሱ ማስታዎቂያዎች ፖስት ይደረጋሉ።እነዚህ ማስታወቂያዎች ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ እና ምንም አይነት ዋስትና የሌላቸው ናቸው። ተከታዮች ወደ ግሩፑ forward ማድረግ እንዳይችሉ ለማገድ ታስቦ ነበር። ነገር ግን ከአጭበርባሪዎች በተቃራኒ ትክክለኛ የስራ ማስታወቂያዎችም ስለሚለቀቁ ተማሪዎች የስራ ዕድል ያገኙበታል። በተጨማሪም በኮሌጁ ውስጥ የአገልግሎት መጓደል ሲኖር ተማሪዎች ሀሳብና አስተያየት የሚሰጡበት ግሩፕ ስለሆነ ተከታዮች ወደ ግሩፑ forward ማድረግ እንዲችሉ ተደርጓል። ስለዚህ ዘላቂ መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስ ሁሉም ተማሪ ራሱን ከሀሰተኛ ማስታወቂያ መጠበቅ ይኖርበታል።

የእነዚህን ሀሰተኛ መረጃዎች አሉታዊ ተፅዕኖ ስንመለከት በሀሰተኛ ደላላዎች የተሸወዱ ሰዎች የሚጎዱበት ዋናው ችግር የገንዘብ ኪሳራ ይሁን እንጅ ከዛም ባለፈ በሐፍረትና ንዴት ችግራቸውን ሳይናገሩ በውስጣቸው ስለሚይዙ ትልቅ የስነልቦና ጉዳት ይደርስባቸዋል። ለምሳሌ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ያጡትን ገንዘብ ለመተካት ሲሉ ውጭ ላይ ያሉ ስራዎችን ያፈላልጋሉ። ስለዚህም ትምህርታቸውን እስከማቋረጥ ሊደርሱ ይችላሉ። የመንግስት ሰራተኞችም ከኪሳራው በተጨማሪ ከቤተሰብ ጋር አለመግባባት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።  

የመፍትሔ ሀሳብ ከአሁን በፊት የተጭበረበሩ ግለሰቦች በማፈር ዝም ከማለት ይልቅ አጭበርባሪዎችን ቢያጋልጡ ቢያንስ በቀጣይ ሌሎች እንዳይሸወዱ ማትረፍ ይቻላል። ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ስልካቸውን፣ አካውንታቸውን እና ቻናላቸውን አጥፍተው የተሰወሩ አጭበርባሪ ደላላዎች በቀጣይም ስማቸውን ቀይረው እንደሚመጡ ጥርጥር የለውም። ሌላው ደግሞ ይህን የማጭበርበር ስራ የሚሰሩ አካላት ከተከፈተ ለረጅም ጊዜ የቆየና ብዙ ተከታይ ያለው ቻናል ወይም ግሩፕ  እየገዙ ራሳቸውን እንደ ትልቅ ድርጅት ያስተዋውቃሉ። ስለሆነም የተከታይ ብዛት አና የተከፈተበት ጊዜ አጭበርባሪ አለመሆናቸውን አያረጋግጥልንም። ስለዚህ ማንኛውም ስራ ፈላጊ አስጠኚ ገንዘብ ከመላኩ በፊት የደላላውን ትክክለኛነት ማረጋጋጥ ይኖርበታል። ከተቻለ ትክክለኛነቱ ከሚታወቅ ደላላ ስራ ለማግኘት መሞከር መልካም ነው። ደላላው የማይታወቅ ከሆነ ግን በቀጥታ ገንዘብ ከማስተላለፍ በፊት የሚሰሩበት ቢሮ የት እነደሆነ በመጠየቅና በአካል ሄዶ በማናገር አሳማኝ ዋስትና እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል ። ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ አዲስ(fresh) ተማሪዎች መረጃው ስለማይኖራቸው ከነባሮች ይልቅ የበለጠ ለመጭበርበር ተጋላጭ ናቸው። ስለዚህ በየትኛውም ዩኒቨርስቲ አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች በትኩረት ማስገንዘብ ይጠበቅብናል።

የ2017 .ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን በተመለከተ የተሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች 

 2017 .12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን በተመለከተ የሚሰራጩ መረጃዎች ከነሐሴ ወር አልፎ መስከረም ወር ላይም ቀጥለዋል። ከእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የአቅም ማሻሻያ ወይም ሪሚዲያልን በተመለከተ ነው። አንዳንዶች በዘንድሮው አመት የሪሚዲያል ትምህርት ፈፅሞ አይኖርም ሲሉ ሌሎች ደግሞ የሪሚዲያል መግቢያ ነጥብ ይፋ ከመደረጉ በፊት ማለፊያ ነጥብ ይፋ ተደርጓል በማለት ሀሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ  ተመልክተናል። እነዚህ ሀሰተኛ ገፆች መረጃውን የሚያስተላልፉበት ዘዴ ከአመታት በፊት የነበሩ ቁጥራዊ መረጃዎችን እና የትምህርት ሚኒስተር መግለጫዎችን የዘንድሮ አስመስሎ በማቀናበር ነው። ለምሳሌ 26,000 በላይ ተከታዮች ያሉት TOBIAS የተሰኘው ሀሰተኛ የቲክቶክ ገፅ መስከረም 10 ቀን በለቀቀው ቪዲዮ "2017 .ም ተፈታኝ ተማሪዎች የሪሚዲያል መግቢያ ነጥብ ይፋ ተደርጓል፤ የመግቢያ ነጥቡም ለተፈጥሮ ሳይንስ(ለወንድ 263 ለሴት 227) እና  ለማህበራዊ ሳይንስ( ለወንድ 220 ለሴት 190) ነው።" በማለት ሀሰተኛ መረጃ አስተላልፏል። ይህ ቪዲዮ ከ 240,000 በላይ እይታ ያለው ሲሆን 600,000 ሪአክሽን እና 3000 የሚጠጋ ሼር አለው። በሚያሳዝን ሁኔታ እንደነዚህ አይነት ሀሰተኛ መረጃዎች በዚህ የሚያበቁ አይደሉም። ይልቁንም ወደፊት የዩኒቨርሲቲ ምደባና ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ቀንን በተመለከተ ተጨማሪ ሀሰተኛ መረጀዎች እየተሰራጩ መቀጠላቸው አይቀርም።

ስርጭት እና ተፅዕኖ ምንም እንኳን ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆኑ ተማሪዎች መረጃው ሀሰተኛ መሆኑን ለመለየት ባይቸገሩም በክፍለ ሀገር ወይም በገጠር አካባቢ የሚኖሩት ወገኖቻችን መረጃው ትክክለኛ ነው ብለው ስለሚያምኑ ለእንደዚህ አይነት ሀሰተኛ መረጃዎች ተጋላጭ ናቸው። እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች የሚገኙት በዋናነት በቲክቶክ ገፅ ይሁን እንጅ  offline እና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ይሰራጫሉ።

አሉታዊ ተፅዕኖዎቹን ስንመለከት ዋናውና አሳሳቢው ሁኔታ የሪሚዲያል መግቢያ ነጥብ አሟልተው ነገር ግን የደረሳቸው መረጃ የተዛባ በመሆኑ ግቢ መግባት እየቻሉ ነጥብ አላሟለሁም ብለው የሚያስቡ ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩ ተማሪዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ አንድ 220 ያመጣ ተማሪ ከላይ የተጠቀሰው ሀሰተኛ መረጃ ከደረሰው መግቢያ ነጥቡ 263 ነው ብሎ በማሰብ ከትምህርቱ ሊስተጓጎል ይችላል። ሌላው ደግሞ ከምደባ ጋር ተያይዞ ብር እያስከፈሉ ምደባ የሚያዩ ግለሰቦች ትኩረታቸው ገንዘብ ላይ ስለሆነ ቦታውን ወይም ዩኒቨርሲቱውን አሳስተው ይናገራሉ። ለአብነት ያክል ባለፈው አመት አለምነሽ ሞላ የተባለች ተማሪ ትክክለኛ የተመደበችበት ዩኒቨርሲቲ ደብረ ታቦር ሆኖ ሳለ በእነዚህ ሰዎች የተነገራት ግን ደብረ ብርሀን እንደሆነ ነበር። ስለሆነም ተማሪዋ ተመድበሻል ተብሎ ወደተነገራት ዩኒቨርሲቲ ከሄደች በኋላ  ተሳስተሻል በመባሏ ለአየር ትራንስፖርት ወጭ እና ለብዙ አንግልቶች ተዳርጋለች።

የመፍትሄ ሀሳብ፦እንደነዚህ አይነት ሀሰተኛ መረጃዎች ሁልጊዜ በየአመቱ የሚከሰቱ ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ልንፈልግ ይገባል። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰው TOBIAS የተሰኘው ሀሰተኛ የቲክቶክ ገፅ ከዚህ በፊትም ገና ውጤት ይፋ ሳይደረግ ነሐሴ ወር ላይ ውጤት ተለቋል በማለት የተዛቡ አሃዛዊ መረጃዎችን በተደጋጋሚ ሲያሰራጭ ተስተውሏል። ፖስት የሚያደርጋቸው መረጃዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ትክክለኛ አይደሉም። ስለሆነም እንደነዚህ አይነት ማህበረሰቡን እየጎዱ ያሉ ሀሰተኛ ገፆችን ሪፖርት እያደረግን አካውንታቸውን ለማዘጋት ሁላችንም የድርሻችን መወጣት ይጠበቅብናል።  የሚያስፈልገንን ትክክለኛ መረጃ በትክክለኛ ሰዓት ባለማግኘታችን ምክንያት የህይወታችን ምዕራፍ ሊበላሽ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። ስለሆነም የምንከተላቸው ገፆች ትክክለኛ እና ታማኝ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን። ለምሳሌ በሀገር ደረጃ ታማኝ ከምንላቸው ገፆች መካከል የመጀመሪያው ቲክቫህ ኢትዮጵያ ነው። ትምህርታዊ መረጃዎችን ብቻ ለሚፈልጉ ለሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይጋለጡ ከ340,000 በላይ ተከታዮች ያሉት Tikvah-universiy የተሰኘውን የቴሌግራም ገፅ እንዲከተሉ ይመከራል። ከዚህም በተጨማሪ official የሆኑ መንግስታዊና ትምህርታዊ ተቋማት ለምሳሌ የትምህርት ሚኒስተር ወይም የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዌብሳይቶችን መከታተል መልካም ነውምደባን በተመለከተ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ እናቀያይራለን የሚሉ አጭበርባሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች ጥሪ ሳያደርጉ ጥሪ ተደርጓል የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ሊሰራጬ እንደሚችሉ  ተገንዝበው ተማሪዎች ከወዲሁ ሊጠነቀቁ ይገባል።

ፓስፖርት ከማውጣት ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የማጭበርበር ስራዎች፦

በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ሀገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ድርቅ፣ ግጭት፣ መፈናቀል፣ ስራ አጥነትና ሌሎች ምክንያቶችን ተከትሎ የሀገራችን ወጣት ከሀገር ለመውጣት ያለው ጉጉት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ወደ ውጭ ለመውጣትም ፓስፖርት ማውጣት አንዱ መስፈርት ስለሆነ ይህንን ፓስፖርት ለማግኘት ብዙዎች በየመስሪያ ቤቱ ደፍ ቀና ሲሉ ይስተዋላል። ነገር ግን ይህንን የሰዎች ከፍተኛ ፍላጎት ተከትሎ አጋጣሚውን በመጠቀም የማጭበርበር ስራ የሚሰሩ እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አሉ። ለምሳሌ የፓስፖርት ቀጠሮ ለማስያዝ፣ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት፣ ለእድሳት፣ ለጠፋባቸው እና ለአጠቃላይ የፓስፖርት ሂደቶች ፈጣን አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ "በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት" ስም የተከፈቱ ሀሰተኛ ገፆች በጣም በርካታ ናቸው። እነዚህ ገፆች የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደወከላቸው አስመስለው ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ። ከነዚህ ሀሰተኛ ገፆች መካከል 200,000 የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት "Ethiopian immigration(ፓስፖርት)" የተሰኘው የፌስቡክ ገፅ እና 88,000 በላይ ተከታዮች ያሉት Ethiopian passport የተሰኘው የቲክቶክ ገፅ እንደ ምሳሌነት ይጠቀሳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በአካል በመገኘት ገንዘብ የሚያጭበረብሩ አሉ። ለምሳሌ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ ወደሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አግልግሎት ዋና መስሪያ ቤት የሚሄዱ ፓስፖርት ፈላጊዎችን ገና ቦታው ላይ ሳይደርሱ ከታክሲ ማውረጃ ላይ ጠብቀው "ኢሚግሬሽን ናችሁ" ብለው በመጠየቅ በሰላምታ ይቀበሏቸዋል። ከዚያ በመቀጠል የወረፋ ችግር ስላለ ፈጣን አገልግሎት እንሰጣችኋለን በማለት ክፍያ እንዲከፍሉ ያሳምኗቸዋል። በዚህ መንገድ የተጭበረበሩ ብዙ ግለሰቦች ሲያዝኑ በተደጋጋሚ አስተውለናል። 

ስርጭትና ተፅዕኖ፦ የእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው። የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስንመለከት ሀሰተኛ ገፆች ቁጥር ስፍር የላቸውም። ሚዲያዎች የቦታ እና የጊዜ ገደብ ስለሌላቸው ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በቀላሉ ይደርሳሉ። በአካል የሚደረገውን የማጭበርበር ስልት ያስተዋልነው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም በሌሎች ከተሞችም ሊኖር ይችላል። ምንም እንኳን መሰረታዊ የዲጅታል እውቀት ያለው ግለሰብ ወይም የአካባቢው ነዋሪ ሀሰተኛ መረጃዎችንና አጭበርባሪ ግለሰቦችን ለመለየት ባይቸገሩም ከክፍለ ሀገር የሚመጡ ወገኖቻችን ግን  በጣም ተጋላጭ ናቸው። 

የመፍትሄ ሀሳብ፦ ዜጎች የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት በር ላይ የሚለጠፉ ትክክለኛ  የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችንና ዌብሳይት መከተል ይጠበቅባቸዋል። በአካል ለሚደረጉ የማጭበርበር መንገዶች ደግሞ በመስሪያ ቤቱ የሚሰሩ ትክክለኛ ባለሙያዎችን ብቻ ማናገር አለብን። ከመስሪያ ቤቱ ውጭ ባለሙያ በመምሰል በመስሪያ ቤቱ ዙሪያ የሚያናግሩ ግለሰቦች አጭበርባሪ መሆናቸውን ተገንዝበን የሚያጭበረብሩትን ግለሰቦችም በአካባቢው ለሚገኙ አስተባባሪ የፀጥታ ሀይሎች በተቻለ ፍጥነት ማጋለጥ ይጠበቅብናል።  

 ያሳለፍነው የመስከረም ወር በርከት ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎችና ዜናዎች የተዘዋወሩበት ወር መሆኑ ይታወቃል። ከእነዚያም መካከል የቤት ለቤት አስጠኚ አገናኝ ነን የሚሉ አጭበርባሪ ደላላዎች፣ የ2017 .12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን በተመለከተ፣ ፓስፖርት ከማውጣት ጋር ተያይዞ የተሰራጩ መረጃዎች በዚህ ሪፖርት ተካተዋል። ነገር ግን ባሳለፍነው ወር የተሰራጩ ሀሰተኛ መረጃ ወይም ዜናዎች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ስለሆነም ማንኛውንም ሀሰተኛ መረጃ ሲያጋጥመን ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጠን በማጋለጥ ማህበረሰባችን ከተለያዩ ጉዳቶች መታደግ አለብን። 

ፀሃፊ: ኤርሚያስ ውበት