ዶናልድ ትራምፕ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያደረጉት ንግግርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወታደሮችን ስለማጓጓዙ የተፈበረኩ መረጃዎች
በመስከረም ወር ውስጥ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ተናግረዋል ተብሎ የተሰራጨ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተጋርቷል። ይህ ቪዲዮ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ተቀናብሮ የተዘጋጀም ነበር።

እነዚህ በረቀቀ መልኩ በቪድዮ፣ በድምፅ እና በምስል ተቀናብረው የሚቀርቡ ስራዎች አንዳንዶቹ ለቀልድ/ስላቅ ተብለው የሚሰሩ ቢሆንም አንዳንዶቹ ሆን ተብሎ ሰዎችን ለማሳሳት እና በዛውም እንደ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ያሉ ጥቅሞች ለማግኘት ታልመው የሚሰራጩ ናቸው።
የ46 ሰከንድ ርዝመት ያለው ቪድዮ ላይ ትራምፕ "ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ... [በጠ/ሚር አብይ] ላይ እንተማመናለን። የተጀመሩትን በማፋጠን እና በትናንሽ እና መለስተኛ ዘርፎች ላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ በጭስ አልባ ኢንደስትሪው ዘርፍ የሚያስገርም ስራ እየሰራ ነው። ቆንጆ እና ንፁህ ሀገር እየመሩ ያሉ መሪ ናቸው" ሲሉ ይደመጣል።(የተሳሳተ መረጃ ቪዲዮ ሊንክ :https://www.facebook.com/share/v/1AMjztUkQZ/)
ቪድዮውን ፌስቡክ ላይ ካጋሩት መሃል 'Qabsaawa Finfinnee' የተባለ ከ61 ሺህ በላይ ተከታታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ይገኝበታል። ይህ የፌስቡክ ማረጋገጫ (blue badge) ያለው ገፅ ያሰራጨው ቪድዮ ከ400 በላይ ግብረ መልስ ያገኘ ሲሆን ከ8,500 በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።
ነገር ግን በGoogle Reverse Image Search እና InVID በመጠቀም የቪዲዮውን ምንጭ በማጣራት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ንግግር በፍፁም እንዳላደረጉ እና ቪድዮው ከትክክለኛ ንግግድ ተወስዶ፣ ድምፁም በቅንብር እንዲገባ ተደርጎ የተመረተ ቪድዮ መሆኑ ተረጋግጧል።
ትክክለኛው ቪድዮ የዛሬ ስምንት ወር ገደማ አንድ አውሮፕላን እና ሄሊኮፕተር ዋሽንግተን አቅራቢያ ተጋጭተው የበርካቶች ህይወት ካለፈ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዜዳንት ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተወሰደ ነው።(የትክክለኛ መረጃ ቪዲዮ ሊንክ
https://www.youtube.com/live/ShRYdYTtIx8?si=lieX_73Nh6SGhhsO)
እዚህ ቪድዮ ላይ ፕሬዚዳንቱ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሲናገሩ አይሰማም። በተጨማሪም በርካታ የድረ-ገፅ አሰሳ ያደረግን ሲሆን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህን ንግግር እንዳደረጉ የሚያስረዳ አንድም መረጃ አልተገኘም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወታደሮችን ወደ ባህርዳር እያጓጓዘ ነው?
ትግራይ ኩሕሎ’ የሚል ስም እና ከ75 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ መስከረም 26/2018 ቀን ሙሉ ወታደሮችን ወደ ባህርዳር ከተማ እያጓጓዘ ነው” የሚል መረጃ አሰራጭቶ ነበር።
ገጹ ይህን መረጃ ከምስል ጋር ያጋራ ሲሆን በምስሉም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ይታያሉ። በገጹ የተጋራዉን የጽሁፍ እና ምስል መረጃ ከ300 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሀሳብ እና አስተያየት የሰጡበት ሲሆን ከ70 በላይ ተጠቃሚዎች መልሰዉ አጋርተዉታል።
ነገር ግን በReverse Image Search የተደረገ ምርመራ እንደሚያመለክት፣ የተጠቀሰው ፎቶ ከተለያዩ ድረ-ገፆች እና ቪዲዮዎች በፊት የተጠቀሰ ስክሪንሽቶች መሆኑ ተረጋግጧል።
ይህ ምስል የተወሰደበትን ቪዲዮ ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሕብረት’ የሚል ስም ያለው ገጽ አንዱ ሲሆን ቪዲዮዉን ከ2 ዓመታት በፊት አጋርቶ ነበር። (የትክክለኛ መረጃ ቪዲዮ ሊንክ https://www.facebook.com/watch/?v=2250405228501839&vanity=100064848901912)

በተጨማሪም ‘The Habesha’ የተሰኘ ድረ-ገጽ ምስሉን በተለያዩ ጊዜያት የተጠቀመ ሲሆን ከዓመት በፊት የሀገር ዉስጥ የአየር ጉዞን በተመለከተ ለሰራዉ ዘገባ ተጠቅሞበት ነበር።(:https://zehabesha.com sharp-increase-in-domestic-air-travel-gains-and-pains/)
እነዚህ የቆዩ ምስሎች ከአውድ ውጪ የቀረቡ ቢሆንም በቅርብ ቀናት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ የመንግስት ሀይሎች እንቅስቃሴ እያረጉ እንደሚገኝ የተለያዩ ሚድያዎች እየዘገቡ ነበር። የቆዩ እና ምንጫቸው ሳይጠቀስ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት ማድርግ ይኖርብናል።
ፀሃፊ:አብዱ አሊ