post-thumb

ከኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ እና በግጭት ቀጣናዎች እንደዚሁም በመስከረም ወር 2018 የተሰራጩ ሌሎች የተሳሳቱ መረጃዎች

ከኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ እና በግጭት ቀጣናዎች እንደዚሁም በመስከረም ወር 2018 የተሰራጩ ሌሎች የተሳሳቱ መረጃዎች

በግጭት ቀጣናዎች ላይ የተሰራጩ ወታደራዊና ፖለቲካዊ የሐሰት መረጃዎች

በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት በሚካሄድባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች (ለምሳሌ በወሎ፣ ጎንደር ወይም ሸዋ አካባቢዎች) “የፋኖ ኃይሎች ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል” ወይም “የመንግሥት ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ ከተሞችን መልሰው ወስደዋል” የሚሉ መረጃዎች ብዙውን ጊዜ የተረጋገጠ የመሬት ላይ መረጃ ሳይኖራቸው የትላልቅ ከተሞችን ስም በመጥቀስ ህዝብን ለማደናገር ይሰራጫሉ።

እነዚህ መረጃዎች ብዙውን ጊዜ የሚመጡት በአንድ ወገን የቆሙና የፕሮፓጋንዳ ዘገባዎችን ከሚያስተላልፉ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ሲሆን፣ እውነታን የማያንጸባርቁ ናቸው።በማህበራዊ ሚዲያ (በተለይም በዩቲዩብ፣ ቲክቶክ እና ቴሌግራም) ላይ ከቆዩ ጦርነቶች ወይም ከሌሎች ሀገራት የተወሰዱ የቪዲዮ ክሊፖችና ፎቶግራፎች በመጠቀምም ወሬውን አጠናክረዋል።

የ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያሉ “ዋና ዋና አዛዦች ከሠራዊቱ ተገንጥለዋል”፣ “እጃቸውን ሰጥተዋል” ወይም “ታስረዋል” የሚሉ ዘገባዎችም ሲሰራጩ ዓላማው በመከላከያ ሠራዊቱ አቅም እና አመራሮች ላይ ጥርጣሬና አለመተማመንን መዝራት ነው።

በግጭት ቀጠና ውስጥ የሚፈፀሙ ሰብአዊ ጥሰቶች የተጋነኑ ወይም ሙሉ በሙሉ የተፈጠሩ ዘገባዎች በተለይም ደግሞ የተሳሳቱ ቁጥራዊ መረጃዎች ተሰራጭተዋል። በአንድ ወገን ብቻ ላይ የሚያተኩሩ እና የሌላውን ወገን ጥፋት ችላ በማለት ጥላቻንና ግጭትን የሚያባብሱ ናቸው።

በመስከረም ወር መጀመሪያ ቀናት በሑመራ ወረዳ (ወልቃይት) የህወሓት ተቃዋሚዎች ከሱዳን በመግባት በጠባቂዎችን እና የአማራ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ቢፈጽሙም በመከላከያና በሚሊሻ የቅንጅት ስራ ተመልሷል በማለት የተሳሳተ መረጃ ተስፋፍቷል። ይህ ሐሰተኛ መረጃ የትግራይንና የአማራ አሁናዊ ሁኔታ በማገናኘት መረጃውን አስተላልፏል፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ከአካባቢው የተገኘ የማስረጃ ምንጮች የሉም።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎትና የተያያዙ ሐሰተኛ ዘገባዎች

የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት ዙሪያ የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎች እና የተጋነኑ ዘገባዎች መሰራጨታቸው በመስከረም ወርም ቀጥለው ነበር። ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ በኃይልና በግዳጅ ለመቆጣጠር እቅድ አላት የሚለው አንዱ  ነው።  የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ የሚገልጸው ፍላጎቷን በሰላማዊ፣ ምክንያታዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ድርድር እና ስምምነት አማካኝነት ለማሳካት መሆኑን ነው። ነገር ግን፣ አንዳንድ የመከላከያ ባለስልጣናትን ንግግር በኃይል ሊቆጣጠሩ ነው በሚል ከፍተኛ ውጥረት እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እንዲባባስ አድርጓል። እነዚህ መረጃዎች በጎረቤት ሀገራት ዘንድ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ጨምረዋል።

አንድ የጎረቤት ሀገር ወይም አካል ለኢትዮጵያ በድብቅ ወደብ ወይም የባህር ኃይል ማሰልጠኛ ስፍራ ሰጥቷታል የሚል መረጃም ተሰራጭቷል። ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ለባሕር በር ተጠቃሚነት እና ለባሕር ኃይል ማዕከል የሚውል የመግባቢያ ሰነድ MOU) መፈረሟ በይፋ ሲታወቅ ይህ ሰነድ በብዙዎች ዘንድ ውዝግብ እና የሐሰተኛ ዘገባ መነሻ ቢሆንም፣ ስለ "ድብቅ" ወደብ የሚወጡ መረጃዎች ግን ብዙ ጊዜ የማረጋገጫ ምንጭ የሌላቸው ናቸው። ከሶማሌላንድ ውጭ ስለተሰጠ "ድብቅ" ወደብ የሚባሉት ዘገባዎች ማስረጃ የሌላቸው ናቸው።

 የአሰብ ወደብን ጨምሮ አንዳንድ አካባቢዎች የኢትዮጵያ እንደሆኑ የሚያሳዩ የተቀየሩ ካርታዎች እና ከሌሎች ቦታዎች የተወሰዱ የውሸት ወደብ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተሰራጭተዋል።እነዚህ ምስሎችና ካርታዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን እና የጎረቤት ሀገራትን ስሜት ለማነሳሳት ሆን ተብለው የተሰሩ የሐሰተኛ መረጃ አይነቶች ናቸው። እነዚህ ዘገባዎች፣ በተለይም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ያደረጉት አንዳንድ ንግግሮች ከበስተጀርባ ሆነው መሆኑ፣ በጎረቤት ሀገራት ዘንድ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እንዲጨምር እና መተማመንን እንዲያሳጣ አድርገዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሃሰተኛ ምስሎችና በግብጽ ዙሪያ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ጋር በተገናኘ ግድቡን የማይገልጹ በኤ.አይ የበለጸጉና የሌላ ሀገር ግድብ ምስሎችን በመጠቀም በመስከረም ወር በሰፊው ተሰራጭተዋል፤ በተጨማሪም በግብፅ በኩል ስለግድቡ የሚቀርቡ የተሳሳቱ መረጃዎች በዚሁ ወር ቀጥለዋል።የግድቡን ግንባታ ሁኔታ በተመለከተ የተዛባ መረጃ ለመስጠት ሲባል፣ ከመጠን በላይ የተጋነኑ (AI-generated) ወይም የግድቡን ሁኔታ ዝቅ አድርገው የሚያሳዩ አሮጌ ወይም የተለወጡ ፎቶዎች ተሰራጭተዋል።

የግእዝ ትምህርት መሰጠት እና የሙስሊሞች በመካነ ሰላም መስጊድ ላይ መሞት

በአማራ ክልል የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የግእዝ ቋንቋን ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ለማስተማር የተላለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያውስጥ  ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ነበር። ይህ ውሳኔ የብዙ ምሁራንን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ተወካዮችን፣ ፖለቲከኞችን እና ግለሰቦችን አስተያየት ያስነሳ ሲሆን፣ በእነዚህ አመለካከቶች መካከል ሐሰተኛ መረጃዎችም ተንጸባርቀዋል። ሰፊ ክፍተት ከፈጠሩ ሐሰተኛ መረጃዎች መካከል፤

● ግእዝ የአማራ ብሔር ብቸኛ ቋንቋ ነው ወይም የአማራ ብሔር የግእዝ ብቸኛ ባለቤት ነው የሚል መረጃ አንዱ ሲሆን የቋንቋ ምሁራን እንደሚሉት፣ ግእዝ የጥንታዊት የአክሱም መንግሥት ቋንቋ ሲሆን፣ ከትግርኛ፣ ትግሬና አማርኛ ቋንቋዎች ጋር ጥብቅ የሆነ ሥር አለው። የቋንቋው ባለቤትነት የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያና የኤርትራ ታሪካዊ ቅርስ ነው።

● ግእዝን መማር ማለት የግድ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ መሆን ማለት ነው ወይም ግእዝን ማስገደድ ሃይማኖትን የመጫን ሙከራ ነው ተብሎ ሲሰራጭ እዝ የቤተክርስቲያን ቋንቋ ቢሆንም፣ የቋንቋ ትምህርት ከሃይማኖታዊ ትምህርት የተለየ ነው። ቢሆንም፣ ተቃዋሚዎች ግእዝ በሃይማኖት ውስጥ ያለው ጠንካራ ቦታ የትምህርቱን ይዘት ገለልተኛ ያደርገዋል ብለው አይቀበሉም። ሐሰተኛ መረጃው ግን ሁለቱን ለይቶ ማየት ባለመቻሉ ተባብሷል።

● ግእዝ የዓለም የመጀመሪያው ቋንቋ ነው" ወይም "ግእዝን የተማረ ሁሉ ሊቅ ይሆናል" የሚለው ሌላኛው የተሰራጨ መረጃ ነው። ግዕዝ  እጅግ ጥንታዊ እና የበርካታ ሰነዶች መገኛ ቢሆንም፣ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ቋንቋ ነው  የሚል የሳይንስ ማረጋገጫ የለውም። እንዲህ አይነቱ አገላለጽ የቋንቋውን ታሪካዊ ጠቀሜታ ከልክ በላይ በማጋነን ለፖለቲካዊ ዓላማ ሊውል ይችላል። በተጨማሪ

የግእዝ ቋንቋ ለግልም ሆነ ለሃገርም አይጠቅምም የሚል መረጃ ሲሰሬጭ በኤ.አይ የበለጸጉ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፎች ተሰርጭተዋል። አጼው ስርዓት አይመለስም፤ የድግምትና የደብተራ ቋንቋ አንማርም የሚሉ ከቋንቋው ጋር የማይገናኙ ሐሳቦችና ያለማስረጃ እንዲሁ የተሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችም ነበሩ።

በመካነ ሰላም 4 ሙስሊሞች መገደላቸውን ተከትሎ ድርጊቱን የፈጸመው አካል ኃላፊነት አልወሰደም፤ ይልቁንስ አንዱ ሌለኛውን በመወቃቀስ ላይ ነበሩ። አብዛኞቹ ግለሰቦች ፋኖን ተጠያቂ አድርገዋል ከዚህ ጋር በተገናኘም የመካነ ሰላሙን መስጅድ ኑርን ፋኖ አቃጠለው ተባለ የሚል የተሳሳተ መረጃ በቲክቶክ ተሰራጭቶ ነበር።

ኢሬቻ በዓል ዙሪያ የታዩ ሐሰተኛ መረጃዎች

በመስከረም ወር ከተከበረው ከኢሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተየያዘም የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎች ተሰራጭተዋል። በተለይም በዓሉ ሀይማኖታዊ ነው ወይስ ባህላዊ፣ የአከባበር ስርዓትና የተከበረባቸው ቦታዎች ላይ እንዲሁም ከሰንደቅ አላማ ጋር በተየያዘ የተሳሳቱ መረጃዎች ተሰራጭተዋል።

ኢሬቻ በአሜሪካ እንዴት እንደተከበረ የሚያሳዩ በኤ.አይ የበለጸጉ ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተሰራጭተዋል።61.6ሺህ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ ገጽ ደግሞ “እሬቻን አስመልክቶ እገዳ ተጥሎበት የዋለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በሰማይ እንቁልልጭ ብሎ ወቷል” በማለት ይህን የቆየ ምስል አጋርቷል።

የሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ከቴክኖሎጂው መዘመን ጋር መልካቸውን ቀይረው እየመጡ ሲሆን ከየትኛውም ጊዜ በላይ የምናገኛቸውን መረጃዎች መመርመር የሚገባን ጊዜ ላይም ደርሰናል።

ፀሃፊ: ደሳለው ጋሻየ