post-thumb

ሃሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎችና የማጭበርበር ስልቶች

በሃገራችን ያለውን የኢንተርኔት ተደራሽነት መስፋፋት እዲሁም የወጣቶችን ስራ አጥነት ተከትሎ የገንዘብ ማጭበርበሪያ ስልቶችና ሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። የማጭበርበሪያ ስልቶች ለመዘርዘር በሚያዳግት መልኩ ቁጥር ስፍር የላቸውም። ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

  •        የባንኮችን ወይም ቴሌኮሙኒኬሽን ስም በመጠቀም የሚያጭበረብሩ አካላት፦ ለምሳሌ "ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ዋና መስሪያ ቤት ነው የምንደውለው እንኳን ደስ አለዎት ሎተሪ ስለደረስዎት የምንነግርዎትን ቁጥሮች ወይም ሊንክ ይንኩ፤ ለሽልማት ዕድለኛ ሆነው ስለተመረጡ ሽልማቱን ለመቀበል ገንዘብ ይላኩልን"  በማለትና የመሳሰሉትን የማታለያ ዘዴዎች በመጠቀም የሚያጭበረበሩ በርካቶች ሲሆኑ በነዚህ ተቋማት ስም የተከፈቱ በርካታ ሀሰተኛ ወይም አጭበርባሪ ገፆች አሉ።
  •       ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ከሚያስፈልጉ ሂደቶች ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የማጭበርበሪያ ስልቶች ፦ ወጣቱ ከሀገር ለመውጣት ያለውን ከፍተኛ ጉጉት ተከትሎ እጭበርባሪዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለምሳሌ ምንም የዲቪ ሎተሪ ማመላከቻ ጊዜ ይፋ ሳይደረግ " የዲቪ ሎተሪ ማመለከቻ ጊዜ ተጀምሯል ሎተሪውን ከእኛ የሞላ የማለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። " በማለት ያጭበረብራሉ። የዲቪ ሎተሪ ተሞልቶ ከተጠናቀቀ በኋላም የሎተሪው አሸናፊዎች  ይፋ ሳይደረግና ከተደረገ በኋላም "የዲቪ ሎተሪ አሸንፋችኋል፣ ከአሜሪካ ኢምባሲ ነው የምንደውለው/ኢሜይል የምንልከው" በማለት ማህበረሰቡን ያታላሉ። ሌላው ደግሞ የ ቪዛ እና የፓስፖርት ሂደት እናስጨርሳለን የሚሉና ብዙ ተከታይ ያላቸው ሀሰተኛ ገፆች በርካታ  ናቸው። በተጨማሪም "ለነፃ የትምህርት ዕድል ወደምትፈልጉት ሀገር እንልካለን" እያሉ የሚያጭበርብሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አሉ።
  •         የባህል ሀኪም ነን የሚሉ አጭበርባሪዎች፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በፌስቡክ እና ቴሌግራም "የባህል ህክምና አገልግሎት እንሰጣለን" የሚሉ አጭበርባሪዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እነዚህ አጭበርባሪዎች መርጌታ የሚል ሀይማኖታዊ ስም የሚጠቀሙ ሲሆን በመድሀኒት ይፈታሉ ተብሎ የማይታሰቡና ያልተለመዱ ጉዳዮችን ለምሳሌ ለገበያ፣ ለስልጣን፣ ለግርማ ሞገስ እና ለሌሎችም ችግሮች መድሀኒት እንሰጣለን በማለት ባለጉዳዩ በባንክ ገንዘብ እንዲያስገባላቸው ያደርጋሉ።
  •       ሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎችና ኤጀንሲዎች፦  በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ የመጣው የሥራ አጥነት ችግር እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የወጣቶችን የስራ እጦት መበራከት ለመቀነስ በሚመስል ሁኔታ በርካታ ሀሰተኛ የሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተፈጥረዋል። እዚህ አጭበርባሪ ኤጀንሲዎች በባዶ ምንም የስራ ማስታወቂያ ሳይኖር ስራ እንዳለ በማስመሰል በየቦታው በወረቀት እና በተለየዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎችን ፖስት ያደርጋሉ። ኤጀንሲዎችም ስራ ፈላጊዎች ስራውን ከማግኘታቸው በፊት ለኤጀንሲው የመመዝገቢያ ወይም የስልጠና በማለት ቅድመ ክፍያ ካስከፈሏቸው በኃላ እንደውልላችኋለን በማለት ይሰናበቷቸዋል። ነገር ግን እነዚያ አጭበርባሪ ኤጀንሲዎች ስራውን ሳያገናኟቸው አድራሻቸውንና ስልካቸውን ያጠፋሉ።   

የእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እና ማህበረሰቡ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ፦   

እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭታቸው ከምናስበው በላይ  እጅግ ከፍ ያለ ነው። መረጃዎች በስፋት የሚሰራጩት በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም የቦታ ገደብ ስለሌላቸው በሌሎች ትልልቅ ከተሞችም በተለያዩ የሀገራችን ቋንቋዎች ይሰራጫሉ። የሚሰራጩበት መንገድ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይ በቴሌግራም፣ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ ሲሆን በየቦታው ወረቀት በመለጠፍም ማስታወቂያዎች ይሰራሉ። ለእንደዚህ አይነት ተግዳሮቶች ጋላጭ የሚሆኑት በስፋት ተመርቀው ወደ ስራው አለም ለመቀላቀል የሚጥሩ ወጣቶች ሲሆኑ ከሚከፈላቸው ደሞዝ ተጨማሪ ገቢ የሚፈልጉ የመንግስት ሰራተኛችም ሰለባ ናቸው።  

የእነዚህን ሀሰተኛ መረጃዎች አሉታዊ ተፅዕኖ ስንመለከት በሀሰተኛ ኤጀንሲዎች ገንዘባቸውን የተበሉ ግለሰቦች የሚጎዱበት ዋናው ችግር የገንዘብ ኪሳራ ይሁን እንጅ ከዚያም ባለፈ የስነልቦና ጉዳት ይደርስባቸዋል። ስራ ፈላጊዎችም የዚህ ጉዳይ ሰለባ መሆናቸውን ተከትሎ ተዓማኒ ኤጀንሲዎች ላይም እምነት እንዳይጥሉ ስለሚያደርጋቸው ትክክለኛ ማስታወቂየዎች ሲወጡም ለስራው ከማመልከት ሊቆጠቡ ይችላሉ። ይህም ሁኔታ ስራ አጥነቱን የበለጠ በማባባስ የከፋ ችግር ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል።

እንደዚህ አይነት የማጭበርበሪያ ስልቶችና ሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎች በዚህ የሚያበቁ ሳይሆኑ  ወደፊትም የሚከሰቱ ናቸው። ስለሆነም ይህንን ችግር ሙሉ ለሙሉ ማቆም ባይቻልም ሁላችንም ሀላፊነት ወስደን የቻልነውን ያህል ለማስታገስ መሞከር አለብን። ለምሳሌ  በተደጋጋሚ ሀሰተኛ መረጃ ወይም ማስታወቂያዎችን ፖስት በማድረግ ማህበረሰቡን እየጎዱ ያሉ ሀሰተኛ ገፆችን ሪፖርት እያደረግን አካውንታቸውን በማዘጋት ሁላችንም የድርሻችን መወጣት ይጠበቅብናልከዚህም በተጨማሪ እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ መረጃዎች ሲያጋጥሙን አምኖ ከመቀበልና ለሌሎች ከማጋራት ይልቅ በመጀመሪያ የመረጃውን ትክክለኛነት ከሚመለከተው አካል ማረጋገጥ አለብን። ሀሰተኛ ሆኖ ከተገኘም ለራሳችን ብቻ መያዝ ሳይሆን ሀሰተኛ መሆኑን ሌሎች ማሳዎቅ ይኖርብናል።

ፀሃፊ: ኤርሚያስ ውበት